ቀጥታ፡

በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡትን ስኬቶች በቴክኖሎጂውም...

በዮሐንስ ደርበው 

ኢትዮጵያ ለፈታኝ ሁኔታዎች የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች። በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ፣ በአረንጓዴ አሻራ ፣ በስንዴ ልማት ፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው። አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ጨምሮ በቴክኖሎጂ መስክም ተወዳዳሪ ሀገርና ወጣት ለመፍጠር ዘርፉ ላይ ኢንቨስት አስፈላጊ እንደመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ነው።

ካለፈውም፤ ከዛሬውም በላቀ ከፍታ ቴክኖሎጂን ነገ የመጠቀም ሁኔታ ስለሚሰፋ በዚህ ዐውድ ንቁ ተዋናይ የመሆንን አዋጭነት በመገንዘብ እንደሌሎቹ ኢንሼቲቮች ለዲጂታሉ ዘርፍ የተሰጠው ትኩረትም በዘርፉ ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ነው።

ለአብነትም፤ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ጅማሮውን ያደረገው የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች አሁንም በነጻ በስፋት እየተሰጠ ነው።

ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ፣ በመረጃ ትንተና፣ በአንድሮይድ ሶፍትዌር ልማት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ትምህርቶች 5 ሚሊየን 5 ሺህ 146 ሠልጣኞች ተመዝግበዋል። ከ3 ሚሊየን የሚልቁት ደግሞ ሥልጠናውን አጠናቅቀዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁሌም በመጠየቅ፣ በመማር፣ አዳዲስ ነገሮችን በመፈለግ ያላቋረጠ ጥረት እየተጉ ለተለዋዋጩ ቴክኖሎጂ ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል።

በላቀ የአየር ትራንስፖርት፣ በኮሪደር ልማት፣ በቱሪዝም፣ በግብርና እንዲሁም በሌሎች መስኮች በምሳሌነት እንደተነሳችው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስም ሆኔ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከፍ ያለ ደረጃ መድረስ ትችላለች።

ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ የመገንባት ሂደት

እንግልትንና ብልሹ አሠራርን መቅረፊያ ብልኀት

የብርቱዎቹ ልጆች ብርታት በቀጣይ

ቶሎ ምልክት የማያሳየው፤ ምልክቶቹ ከታዩ በኋላም ወዲያው ካልታከመ ለአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የሚዳርገው በሽታ

ባሳለፍነው ጥር ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ሲካሄድ፤ በሪፎርም ሥራችን ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እያደረግን ያለነው በዘርፉ ተወዳዳሪ ሀገርና ወጣት ለመፍጠር ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ከአምሥቱ ብዝኃ ዘርፎች አንደኛው ቴክኖሎጂ የሆነበት ምክንያት ነገ ለትውልድ ካለው ፋይዳ አንጻር መሆኑንም አጉልተዋል።

ለዚህም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በማሳያነት ጠቅሰው፤ የዛሬ ሥድስት ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ስታቋቁም አንድም የአፍሪካ ሀገር በተቋም ደረጃ ኤ አይ አለመፍጠሩን በማንሳትምኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እየገነባች መሆኗን እና ቢበዛ እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ሥራ እንደሚጀምርም መጠቆማቸው ይታወሳል።

ይህ ሁሉ ዝግጅት የሚደረገው አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን በጊዜው መሥርተው ዛሬ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆነው፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይልንም በጊዜው መሥርተው ዛሬ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል ከሚባሉት አንዱ እንደሆነው ሁሉ፤ ነገም የእኛ የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ እና ተቋም በአፍሪካ ውስጥ ስመጥር መሆን እንዲችል፣ የተስተካከለ መሠረት ይዞ እንዲነሳ በሪፎርም ውስጥ አንደኛ ቁልፍ ጉዳይ አድርገን ስንሠራ ቆይተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ለተሻለ ነገ እየተደረጉ ካሉ በርካታ ዝግጅቶች አንዱ፤ በግል ቢሆን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቀውን የ5 ሚሊየን ኮደሮች ሥልጠና መንግሥት በነጻ ማቅረቡ ይገኝበታል።

ይህ ኢኒሼቲቭ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ስኬታማ በመሆኑ፤ ውድ ኢትዮጵያውያን ለ5 ሚሊየን ኮደሮች ምዕራፍ ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።

በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት የታቀደውን ግብ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ማሳካት ተችሏልም ብለዋል። ይህ ስኬት የሕዝባችንን ቁርጠኝነት እና ወሰን የሌለው ዐቅም ማረጋገጫ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከዛሬ 10 ዓመት ገደማ ጀምሮ ዓለም ለሥራ ከሚፈልጋቸው ሰዎች መካከል ከሞላ ጎደል 50 በመቶው የሚገኘው አፍሪካ ውስጥ እንደሚሆን በማመላከት፤ ይህንን ዕንቁ ዕድል በወጉ ተረድቶ ወጣቱን ለነገ ውድድር ማዘጋጀት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ሪፎርም ምን ያህል ትውልድ ላይ አበክሮ እንደሠራ ለማየት አንዱ መገለጫ ቴክኖሎጂ መሆኑን እንገነዘባለን።

ስለዚህ በዲጂታሉ ዓለም በልኩ ለመዘጋጀት የጀመርነው ታሪካዊ ምዕራፍ የጉዟችን ማብቂያ ሳይሆን ብሔራዊ ርዕያችንን ይበልጥ የምናፋጥንበት መነሻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም. ድረስ የሠልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊየን ለማድረስ የተሰነቀውን ግብ ለማሳካት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ ተልዕኮ አካል እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክትም በመጭው የክረምት ወቅት ጊዜያችሁን በዋዛ ከማሳለፍ ተቆጥባችሁ፤ በመመዝገብና በመማር ወደ ትምህርት ገበታችሁ ስትመለሱ ተማሪዎች ብቻ ሳትሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላችሁ የዲጂታል መሪዎች እንድትሆኑ አሳስባለሁም ብለዋል።

በሌላ በኩል ባሳለፍነው ታኅሣሥ ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ከምሁራን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ፤ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ከተማርን፣ ዝግጁ ከሆንን፣ እየሠራናቸው ያሉትንና በቀጣይ የምናከናውናቸውን ጨምሮ በመተባበር ለለውጥ ዝግጁ ሆነን በትጋት ከሠራን፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሂደት የማይናቅ ደረጃ ላይ እንደርሳለን ብለዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በታኅሣሥ ወር በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽ፣ ፍትሐዊ እና አስተማማኝ የዲጂታል ምኅዳር መፍጠር ላይ ማተኮሩን አስታውቀዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬታማ እንደነበር አውስተው፤ ለማሳያነት ያህል በሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ-ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባል ደረጃ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት መሸጋገሯንም እንዲሁ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030፤ ተደራሽነትን ማስፋት፤ እኩል ዕድል ማመቻቸትና በተቋማትና ሕዝብ መካከል መተማመንን መፍጠር የተሰኙ ሦስት ቁልፍ ትልሞችን ሠንቆ በትግበራ ላይ ይገኛል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት ተቋም መገንባቱንም አረጋግጠዋል በወቅቱ። ይህም ለዲጂታል 2030 ስኬታማነት የራሱን ሚና ያበረክታል ነው ያሉት።

የትውልዱ የዲጂታል አጠቃቀም ከኢትዮጵያ ባሕል፣ ዕሴትና ሉዓላዊነት ጋር በተናበበ መልኩ ሊሆን እንደሚገባም መክረዋል።

ቴክኖሎጂን ጨምሮ በተለያዩ በርካታ መስኮች ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር በመሪነት ስኬታማ ተግባራት እያስመዘገቡ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል። ሹመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ላሳዩት አመራር እና ሀገራቸው በአኅጉሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ለምትገኘው የላቀ ሚና ዕውቅና የሰጠም ነው። ይህም ልክ እንደሌሎች መስኮች በቴክኖሎጂው ዘርፍም በትክክለኛው መንገድ እየተጓዘች መሆኗን ይመሠክራል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ፤ ከእርሻ እስከ ፍርድ ቤት፣ ከመንገዶች እስከ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድረስ፤ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ እና ዜጎችን ማዕከል ያደረጉ አገልግሎቶችን የሚሰጥ የዲጂታል ሥነ-ምኅዳር እየገነባች ነው።

ለዚህ ደግሞ የሚሠራው ሁሉ ለበለጸገች ኢትዮጵያ ነውና መንግሥትን ማገዝ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት፣ ለሀገር የሚበጀውን በተነሳሽነት ለመፈጸም በይበልጥ ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል።

ሀገር በቴክኖሎጂ ስትልቅ የሕዝቡ የኑሮ ዘይቤ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ አገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ ሰው ተኮር ጉዳዮች ቀላል፣ ፈጣን እና ምቹ እንደሚሆኑም መገንዘብ ይገባል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂና ፋይዳዎች እንደሚያመላክቱት እንደ ሀገር በዘርፉ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው።

በቀጣይ በቴክኖሎጂው መስክ ከዓለም ጋር እኩል ለመሄድ እንዲቻል፤ በነጻ እየተሰጠ ያለውን የ5 ሚሊየን ኮደሮች ሥልጠና አጠናክሮ በመቀጠል ዜጎች ልንጠቀምበት ይገባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የምትገነቡት ነገ የሚጀምረው ዛሬ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም