የጤና ነገር - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ነገር
በዮሐንስ ደርበው
ቶሎ ምልክት የማያሳየው፤ ምልክቶቹ ከታዩ በኋላም ወዲያው ካልታከመ ለአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የሚዳርገው በሽታ …
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች ውጤቶች እንደሚያመላክቱት ከሚወለዱ 2 ሺህ ሕጻናት መካከል አንዱ የታይሮይድ ሆርሞን ሳይኖረው ይወለዳል።
ለመሆኑ የታይሮይድ ሆርሞን አስፈላጊነት ምን ያህል ነው? ባይኖርስ ምን ይከሰታል?
በወቅቱ ካልታከመ እስከ አዕምሮ ህመም የሚያደርሰው የታይሮድ ሆርሞን እጥረት (አለመኖር) በሚያስከትላቸው ችግሮችና ቀድመው ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄዎች ላይ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የሕጻናት፣ የስኳር ህመም እና የሆርሞን ችግሮች ሰብስፔሻሊስት ዶክተር ፍቅር መሠረት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ አብራርተዋል።
· የታይሮይድ ሆርሞን ምንድን ነው?
እንደባለሙያዋ ገለጻ፤ የታይሮይድ ሆርሞን ታይሮይድ ዕጢ ከሚባለው የአካል ክፍል የሚመነጭ ሆርሞን ነው።
በሰውነታችን ውስጥም እጅግ አስፈላጊ ከምንላቸው ሆርሞኖች አንዱ ነው ይላሉ። ጠቃሚነቱን ሲያስረዱም፤ በተለይም ሕጻናት ላይ ለአዕምሮ ዕድገት፣ ለሰውነት ዕድገት እንዲሁም እያንዳንዱ ኅዋሳችን የታይሮይድ ሆርሞንን ለሜታቦሊዝም (ሰውነታችን ኃይል ማመንጨት እንዲችል) ይጠቀምበታል ብለዋል።
· የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት መንስዔዎች
መንስዔዎቹን በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል ጠቁመው፤ አንደኛው ሲወለዱ ጀምሮ የሚከሰት የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት ሲሆን ሁለተኛው ልጆች ካደጉ በኋላ በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚከሰት መሆኑን አብራርተዋል።
አንደኛው፤ ሕጻናት ሲወለዱ ጀምሮ የታይሮድ ሆርሞን እጥረት የሚከሰትበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቅሰው፤ ለዚህም ከሚነሱት ምክንያቶች አንዱ የታይሮይድ ዕጢ አለመፈጠር መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ጽንስ በማሕጸን ውስጥ ሆኖ ዕድገቱ ቀጥሎ ሳለ፤ በአንጻሩ የታይሮይድ ዕጢ በአግባቡ ሳያድግ ይቀርና የሚፈለገውን ሆርሞን እንዳያመነጭ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል ብለዋል።
አክለውም፤ ዕጢው መቀመጥ ባለበት ተገቢ ቦታ ላይ በትክክል ሳይቀመጥ ሲቀር በሆርሞን ማመንጨት ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል የታይሮይድ ዕጢ የተለያዩ የዕድገት ደረጃዎችን አልፎ ሆርሞን እንደሚያመነጭ ገልጸው፤ በአንዱ ደረጃ ላይ ዕክል ቢያጋጥመው ሆርሞን ማመንጭት እንደማይችል አስረድተዋል።
ሁለተኛው፤ ልጆች ካደጉ በኋላ ለሚከሰተው የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት (አኳየርድ) ደግሞ ምክንያቱ፤ የታይሮይድ ዕጢ በነጭ የደም ኅዋሶች ሲጎዳ መሆኑን አስረድተዋል።
· በታይሮይድ ዕጢ ላይ የሚከሰቱ ችግሮች
የተለያየ ዓይነት የታይሮይድ ዕጢ ችግር ሊኖር እንደሚችል የገልጹት ዶክተር ፍቅር፤ የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት፣ የታይሮይድ ሆርሞን መብዛት፣ የታይሮይድ ዕጢ ማደግ (ጎይተር)፣ የታይሮይድ ሆርሞን ካንሰር የሚሉትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በአብዛኛው በሕጻናት ላይ የሚያጋጥመው የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት መሆኑንም በማስረዳት።
· የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት በሕጻናትና በአዋቂዎች
የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት በሕጻናት (ኮንጅናይታል የሚባለው ኬዝ) እና በአዋቂዎች (አኳየርድ የሚባለው ኬዝ) ዘንድ እንደሚከሰት ዶክተር ፍቅር አስገንዝበዋል።
በዚህም መሠረት በሕጻናት ላይ በአብዛኛው የሚከሰተውም፤ ሲፈጠሩ ጀምሮ የዕጢው አለመኖር፣ የዕጢው በትክክለኛ ቦታው ያለመቀመጥ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዋቂዎች ዘንድ የሚከሰተው ደግሞ በአዮዲን እጥረት እንዲሁም የታይሮድ ዕጢ በነጭ የደም ኅዋሶች መጎዳት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
· የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት ምልክቶች ምንድን ናቸው? ኬዙ ያለባቸው ሕጻናትንስ መቼ ወደ ሕክምና ተቋም ይሂዱ?
የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት ሲኖር እንደሌሎች በሽታዎች አጣዳፊ ምልክቶች እንደሌሉት የሚገልጹት ዶክተር ፍቅር፤ ምልክቶቹ ቀስ በቀስ የሚመጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለምሳሌ፡- የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት ኖሯቸው ከሚወለዱ ሕጻናት መካከል አብዛኞቹ በመጀመሪያዎቹ አንድ/ሁለት ሳምንት ምልክት ላያሳዩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ይህም በመሆኑ በተለያዩ ሀገራት የሕጻናት ቅድመ ምርመራ እንደሚደረግ አመላክተዋል። ምክንያቱም የታይሮይድ ሆርሞን እጥረትን ቀድሞ ማወቅ መከላከል የሚያስችለው የጎንዮሽ ጉዳት ስላለ ነው ይላሉ።
በሕጻናት ላይ በመጀመሪያው ወራቸው ከሚታዩ ምልክቶች መካከልም፤ ረጅም ሠዓት መተኛት፣ ጡት የመጥባት ፍላጎት አለመኖር፣ የሰገራ መድረቅ፣ በአንዳንድ ልጆች ላይ የፊት፣ የሆድ አካባቢ፣ ዕጅና እግር ማበጥ፣ ከሁለት ሳምንት በላይ የሚቆይ የቆዳ ቢጫ መሆን የሚሉት እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
ይህን ተከትሎ በወቅቱ ወደ ሕክምና መውሰድ ካልተቻለ ግን ይላሉ፤ የዕድገት መዘግየት ምልክት እንደሚታይ አስረድተዋል። መቀመጥ፣ መቆም፣ መራመድ፣ መናገር፣ … የሚሉትን ጨምሮ ከዕድሜ ክልላቸው እና ከሚጠበቅባቸው አንጻር ካነሱ (ዕድገታቸው በሁሉም መንገድ ወደ ኋላ ከቀረ) የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት እንዳለመ መገንዘብ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም፤ የቆዳ መድረቅ፣ የፀጉር መነቃቀል፣ ቀልጣፋ አለመሆን (መፍዘዝ)፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ እና ከዕድሜ አንጻር የቁመት ማጠር ዋና ዋና ምልክቶቹ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።
· አሳሳቢነት
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ጥናቶች ውጤቶች እንደሚያመላክቱት፤ ከሚወለዱ 2 ሺህ ሕጻናት መካከል አንዱ የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት ይኖርበታል።
እንደ ዓለም በአጠቃላይ ካሉ ሕጻናትም ከ 1 እስከ 2 በመቶ ያህሉ የታይሮድ ሆርሞን እጥረት ተጠቂ መሆናቸውን አንስተዋል።
· ምክረ ሐሳብ
በማኅበረሰብ ደረጃ በልጆች ላይ ያልተለመደ (የተለየ) ምልክት ሲታይ ሁሌም የሕክምና ባለሙያ ማማከር አስፈላጊ መሆኑን መክረዋል።
የታይሮይድ ሆርሞን እጥረትን ቀድሞ አለማወቅ (በተለይም እስከ 5 ዓመታቸው ድረስ ታውቆ ሕክምና ካልተጀመረ) የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እንደሚያስከትል የገለጹት የሕክምና ባለሙያዋ፤ ወላጆች፣ አሳዳጊዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ልንከላከላቸው ከምንችላቸው የአዕምሮ ዝግመት መንስዔዎች መካከል የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በተለያዩ ሀገራት የሕጻናት ቅድመ ምርመራ የሚሠራው ለዚሁ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ጎበዝ ተማሪ ሆነው ውጤታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ከሆነ፣ የቁመት ማጠር ካለ፣ የሰገራ መድረቅ ካለ፣ ለመጫዎት እና ለመመገብ ፍላጎት ካላሳዩ፣ የቆዳ ድርቀት፣ የጸጉር መነቃቀል ሲኖር የታይሮድ ሆርሞን እጥረት ሊሆን ስለሚችል አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግን መክረዋል።
የታይሮይድ ሆርሞን እጥረት በቀላሉ ሙሉ በሙሉ መታከም ይችላል፤ ነገርግን ዛሬ ነገ በሚል መዘናጋት እና ምልክቶችን ባለማስተዋል በሽታው ወደ ሌላ ህመም የመሸጋገር ዕድል ስለሚኖረው ሕክምናውም በዚያው ልክ ውድ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
#Ethiopian_News_Agency
#የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት
#የጤና_ነገር