ቀጥታ፡

እንግልትንና ብልሹ አሠራርን መቅረፊያ ብልኀት - መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

በኢዜአ ዐይን …!
 
በዮሐንስ ደርበው

እንግልትንና ብልሹ አሠራርን መቅረፊያ ብልኀት - መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለእንግልትና ብልሹ አሠራር አጋላጭ ሁኔታዎች ይስተካከሉን የሚሉ እሮሮዎች በተለያዩ ሕዝባዊ ውይይቶች ሲነሱ ቆይተዋል።

በተለይም በአንዳንድ ተቋማት መንግሥታዊ አገልግሎት ለማግኘት እዚያም እዚህም መንከራተት፤ደግሞም ወረፋ በመጠበቅ መጉላላት ብሎም ለጊዜና ገንዘብ ወጪ መዳረግ ይስተዋላል የሚሉ ሐሳቦች ተስተጋብተዋል።

ሾተላይ ምንድነው? እንዴትስ ይከሰታል? ቀድሞ መከላከልስ ይቻላል?

ባሳለፍነው ሳምንት …

መንግሥትም የተነሱ ቅሬታዎችን ማረቅ የሚያስችል አሠራር በመንደፍ ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንድ ብሎ አስጀመረ።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ማዕከሉ አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅትም ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው ብለው ነበር።

አሁን ላይም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሁን በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ ነው።መስፋፋቱም በማዕከላት ብዛት፣በአገልግሎት መስጫ መስኮቶች ቁጥር እና በአገልግሎት ዐይነቶች እየተገለጠ ነው።

በዚህም በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 2 ሺህ 260 አገልግሎቶች በአንድ ቋት የተደራጁ ሲሆን ይህ አሃዝም ለዘርፉ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት እና ያለውን ፈጣን እድገት ያመላክታል።
 
ጉዳዩ የዜጎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ማላቅ፤ ብልሹ አሠራርንም መቅረፍ ነውና መንግሥት በልዩ ትኩረት ይዞታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድሬዳዋ አሥተዳደርና በሐረሪ ክልል ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትም፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን የምልከታቸው አካል ማድረጋቸው ለጉዳዩ የተሰጠውን ከፍያለ ትኩረት ያሳያል።
 
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሶብ የሞባይል አገልግሎትን በመረቁበት ወቅት ደግሞ፤ ካቀድናቸው አምስት የልማት ምሰሶዎች መካከል ቴክኖሎጂን ለአገልግሎት ዘርፉ እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናንና ተደራሽነትን ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሠራን ነው ብለዋል።
 
አክለውም፤በመሶብ አገልግሎቶች የታየው ከፍተኛ የደንበኞች ዕርካታ የዚህን የሥራ ሞዴል ውጤታማነት በግልጽ አረጋግጧል፤ ይህም አሠራሩን ይበልጥ ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ተናግረዋል።
 
ዜጎቻችን ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ትርጉም ያለው የጊዜ ቁጠባ እንዲያገኙ ለማስቻል፤ እነዚህን የተቀናጁ አገልግሎቶች ይበልጥ ተደራሽ የማድረግ ሥራችንን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
 
በተመሳሳይ በዚሁ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባጋራው መረጃ መሶብ ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት፤ አስፈላጊ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀጥታ ወደ ማኅበረሰቡ ለማድረስ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው ብሏል። የስምንት ተቋማትን አገልግሎት በአንድ ላይ በማቀናጀት፣ ዜጎች ረጅም ርቀት ሳይጓዙ ወይም የተለያዩ ቢሮዎችን ማንኳኳት ሳያስፈልጋቸው ምቹ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ የሆነ መፍትሔ ይሰጣል ማለቱም ይታወቃል።

የፌዴራል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አንተነህ ማሞ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ደግሞ፤ ዘመናዊና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት ምኅዳር በመፍጠር የተገልጋዮችን እርካታ ማረጋገጥ ያስቻለ ስኬት ተገኝቷል ብለዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶችም ዜጋ ተኮር፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍልና የተገልጋዮችን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዲጂታል 2030 የአገልግሎት አሰጣጥ አመላካች ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱ 50 ሀገራት መካከል አንዷ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዜጎች መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በኦንላይን በየትኛውም ቦታ ሁሉንም አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ ስለመሆኑም እንዲሁ።

አገልገሎቱን ያገኙ አስተያየት ሰጭዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንግልትን ያስቀረ፣ ጊዜና ወጭን የቀነሰ ነውና ይስፋፋ፤ ተጠናክሮም ይቀጥል።
 
#መሶብ_የአንድ_ማዕከል_አገልግሎት #የዜጎችን_እንግልትና_ብልሹአሠራርን_መቅረፍ
 
#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ #በኢዜአ_ዐይን

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም