ከሀገራዊ ለውጡ አበርክቶዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገራዊ ለውጡ አበርክቶዎች
በዮሐንስ ደርበው
የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያን ማሥተዳደር ከጀመረ እነሆ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ላይ 8 ዓመት ሞላው። በእነዚህ ዓመታት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ ዘርፉ በዲፕሎማሲውና በሌሎችም መስኮች የተለያዩ ስኬቶች ተከናውነዋል።
በእነዚህ ጥቂት ዓመታትም ለማሳካት ቀርቶ ለማሳብ የማይደፈሩ ብዙ ውጤቶችም ተመዝግበዋል። የተገኙት ስኬቶች ከጊዜያቸው የፈጠኑ ናቸው።
ለዚህም ሕዝቡ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በነቂስ እየወጣ አድናቆቱን ገልጿል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሰጡት የሰላ አመራርነትና ቁርጠኝነትም አክብሮቱንና ምሥጋናውን ገልጿል።
የለውጡ መንግሥት አካሄድ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የልማት ፕሮጀክቶችም በይበልጥ ተስፋፍተውና ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግሥት ለሚያደርገው ጥረት ከጎኑ እንደሚቆሙም በድጋፍ ሰልፍ ላይ ባስተጋቧቸው መልዕክቶቻቸው አረጋግጠዋል።
በአጠቃላይ በለውጡ መንግሥት ለማሳካት ቀርቶ ለማሰብ የማይደፈሩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከእነዚህ ከፍተኛ ጥቅም ከተገኘባቸው የታሪክ እጥፋትን ካሠረጹ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ጥቂቶቹን ቀጥለን በወፍ በረር እንዳሥሣለን።
የዘርፉ ባለሙያዎች ‘ካሎሪ አልባው መድኃኒት’ ይሉታል።
• የኮሪደር ልማት
እንደምናውቀው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነትና ልዩ ትኩረት የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከሁሉም አስቀድሞ የተጀመረው በአዲስ አበባ ከተማ ነው። አሁን ላይ ደግሞ በመላ ሀገሪቱ የበርካታ ከተሞችን ገጽታ የቀየሩ አስደማሚ ሥራዎች ተከናውነውበታል። ይህም በገጠር ጭምር ተጠናክሮ የቀጠለ ጉዳይ ነው።
ለዘመናት አሮጌ ገጽታዋን ይዛ ያሸለበችውን አዲስ አበባ እንደ አዲስ የፈጠራትም ይኸው ፕሮጀክት ነው። አሁን ላይ መዲናይቱ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች የአዲስ አበባን ለውጥ ዐይተው ዝም ማለት አልቻሉም። ከመደመማቸው አንጻር የዘወትር አጀንዳቸውም እያደረጓት ይገኛሉ።
ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት፤ ኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ነው ማለታቸው ይታወሳል። ከከተሜነት ዕድገት ጋር የተሣሠረ ልማት መሆኑንንም አስረድተዋል።
ከለውጡ መንግሥት ዐበይት የትኩረት መስኮች አንዱ የሆነውን የቱሪዝም ዘርፉን እንቅስቃሴ ለማሳደግም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ድርብርብ ፕሮጀክት ነው የኮሪደር ልማት።
• የበጋ መስኖ
የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የለውጡ መንግሥት ዋነኛ ትኩረቱ ነው። ለዚህም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን አንዱ ማሳኪያ ሥልት አድርጎ እየተጋ ይገኛል። የበጋ መስኖ ስንዴ ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት አቁማ መላክ እንድትጀምር ያስቻለ ኢኒሼቲቭ ነው። በዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችና በሜካናይዜሽን ታግዞ በስፋት እየተሠራበትም ይገኛል።
ከለውጡ መንግሥት ወዲህ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ምክንያት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በምርታማነት ማደግና የሥራ ዕድል በመፍጠር አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል። የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብም ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶበታል።
ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ላይ ባሳየችው ትጋት፤ ፍጆታዋን በራሷ ዐቅም የሸፈነችው፣ ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ያቆመችው፤ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ የጀመረችው በለውጡ መንግሥት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም (ዶ/ር) በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳሊያ በመሸለም ለጥረታቸው ዕውቅና መስጠቱም ይታወሳል።
• መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት
ቀደም ሲል አንድ ጉዳይን ለማስፈጸም እዚያም እዚህም መንከራተት የግድ ነበር። በዚህ አያበቃምና ወረፋውም ሌላ ችግር ነው።
መንግሥት በተለያዩ መድረኮች ባካሄዳቸው ሕዝባዊ ውይይቶች ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ለእንግልትና ብልሹ አሠራር አጋላጭ ሁኔታዎች ይስተካከሉልን የሚሉ እሮሮዎች በረከቱ። መንግሥትም የተነሱ ቅሬታዎችን ማረቅ የሚያስችል ሥራ ወደ ተግባር አሥገባ።
በዚህም መሠረት ሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አንድ ብሎ ጀመረ። በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዜጎቻችን ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነውም አሉ።
ለዚህ ቁርጠኝነታችን አንዱ ማሳያ የሆነውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስጀመራቸውንም ገለጹ።
እንግዲህ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፤ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ አንድ ማዕከል በመሰብሰብ በቴክኖሎጂ ታግዘው በተሳለጠ ሂደት እንዲሰጡ በማድረግ የተገልጋይን እንግልት፣ ገንዘብ እና ጊዜ መቀነስ ያስቻለ አሠራር ነው። እንግልትንና ብልሹ አሠራርን መቅረፊያ ብልኀት ተደርጎም ይወሰዳል። በየከተሞቹም እየተስፋፋ ነው።
• አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤ አይ)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተወዳዳሪ እና ተጠቃሚ እንድትሆን ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው በቁጭት በተለያዩ መድረኮች ያነሳሉ። ለዚህም መፍትሔ ዘይደው ተቋማትን ከማቋቋም ጀምሮ ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ተግተዋል።
በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ከቴክኖሎጂው ጋር አብሮ ለመጓዝ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን አቋቋመች። የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ በመክፈት በግብርናው፣ በጤናው እና በሌሎችም ዘርፎች የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠርም በሂደት ላይ ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት ቀይሮ ወደ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ሕንፃ በተዛወረበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአምስት ዓመት ውስጥ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ መድረሱ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ የሮቦቶችን ሶፍትዌር ብቻ ሳይሆን ውጫዊ የአካል ክፍልን (ሃርድዌር) መሥራት ጀምሯል ብለዋል።
ድሮን ማምረት ብቻ ሳይሆን የማነጋገር ዐቅም እየፈጠረ ያለ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል።
አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በአፍሪካ ደረጃ የሚወዳደር አሠራርን የሚከተል መሆኑን ጠቁመው፤ በርካታ ምርቶችን አውጥቷል ማለታቸው ይታወቃል።
ብንፈልግም ባንፈልግም ራሳችንን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሂደት ውስጥ ማስገባት ካልቻልን ደረጃው የትም ቦታ ይሁን እንደ ሀገር እንደ ከዚህ ቀደሙ ከትላልቅ ሪቮሉሽኖች ወደ ኋላ እንቀራለን ሲሉ ማስገንዘባቸውም ይታወሳል።
• የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር
የዓየር ንብረት ለውጥ የምድራችን ፈተና ነው። ልብ መባል ያለበት ግን አፍሪካ ለዓየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዋ አነስተኛ ሆኖ ሳለ ጉዳቷ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ስለዚህ አኅጉሪቱ ዕጇን አጣጥፋ ወቃሽና ጠባቂ ከመሆን ይልቅ፤ በፈተና ውስጥ ሆናም በዘላቂነት የዓየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ለማምጣት መትጋት አለባት። የሩቅ መፍትሔ አይጨበጥም፤ አይዘልቅምና።
ከመፍትሔዎች አንዱ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሚወደስ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት፤ በ2011 ዓ.ም በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ለዓየር ንብረት ለውጥ ከተሰጡ ምላሾች መካከል በፊታአውራሪነት ይጠቀሳል።
በተደራጀና ተቋማዊ ሆኖ ባልተቆራረጠ አካሄድ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከተተከሉ ችግኞችም በየዘርፉ ተጠቃሚነት አድጓል፤ ተጠናክሮም ይቀጥላል።
• የሌማት ትሩፋት
ከመጋቢት ሥጦታዎች አንዱ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ነው። የምርት አቅርቦትን በማስፋት ለተረጋጋ ግብይት እና ለተመጣጠነ ሥርዓተ-ምግብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከት ላይም ይገኛል።
ኢኒሼቲቩ ለግብርና ኢንቨስትመንትና ለሀገራዊ የሥርዓተ-ምግብ መሻሻል ጉልኅ ሚና እየተጫወተ ነው። የዋጋ ንረትን በማረጋጋት፣ የምርት ስብጥርን በማሳደግና በዘላቂነት በማቅረብ ረገድም የጎላ ሚና አለው።
የግድ ሰፋፊ መሬት መፈለግ ሳያሻ በትንሽ ቦታ ብዙ በማምረት ፍጆታን ከመሸፈን አልፎ ኢኮኖሚን በመደጎም እና የሥራ ዕድል በመፍጠርም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።
• የቱሪስት መዳረሻ ልማት
ቅርሶች እንዲጠገኑ፣ አዳዲስ ሎጂዎች እንዲገነቡ፣ በመዳረሻ ስፍራዎች መሠረተ-ልማት እንዲሟላ ያስቻሉ ተግባራት በለውጡ መንግሥት ተከናውነዋል፤ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ እና ስኬታማ ኢኒሼቲቭ ነው።
በዚህ ሂደት ከሐሳብ አመንጭነት ባሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የጻፉትን መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ጭምር ለቅርስ ጥገናና ለቤተ-መጻሕፍት ግንባታ እንዲውል አድርገዋል።
በተጨማሪም የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማልማትና ለማስፋፋት፤ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የተሰኙ ትላልቅ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ወደ ተግባር አስገብተዋል።
በእነዚህ ኢኒሼቲቮች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል። ትሩፋታቸውም ሰፊ አበርክቷቸውም በርካታ ሆኖ ብቅ ብሏል። አማራጭ የቱሪስት መዳረሻም ሆነዋል።
• የተቋማት ግንባታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥር 7 ቀን 2018 ዓ.ም “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” በሚል መሪል ሐሳብ በተካሄደው የዐበይት ተቋማት አፈፃፀም ግምገማ ኮንፈረንስ ላይ፤ የተቋማት ግንባታና ዝግጁነትን ማረጋገጥ የመንግሥት ዐበይት ኃላፊነቶች ናቸው ብለዋል።
በዚህ የተነሳ ነው የሀገራችንን የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማጠናከር የታሰበባቸው ሰፋፊ እርምጃዎችን የወሰድነው ሲሉም አስገንዝበዋል በወቅቱ።
ዘመን የማይለውጣቸው ዘላቂ ጠንካራ ሃገራዊ ተቋማትን በመገንባት ረገድ ብዙ ርቀት መጓዝም ተችሏል። በመሆኑም የመንግሥት ተቋማት ምቹ የሥራ ከባቢ እንዲሆኑ በማድረግ እና ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር የማይፈርሱ ወይም የሚሻገሩ ተቋማት መገንባት ተችሏል። ይህ ትጋት ተጠናክሮም ቀጥሏል።