ቀጥታ፡

የጤና ነገር ...

በዮሐንስ ደርበው

የዘርፉ ባለሙያዎች ‘ካሎሪ አልባው መድኃኒት’ ይሉታል።

የኒውትሬሽን ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የሰው ልጅ የሰውነት ክፍል 60 በመቶው ውኃ እንደመሆኑ ለተስተካከለ ጤና ሚዛን መጠበቅ በቂ ውኃ መጠጣት ይገባል።

ውኃን በትክክለኛው መጠንና ጊዜ መውሰድ ከተቻለ የኩላሊት ህመም ተጋላጭነትን 50 በመቶ መቀነስ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ።

ነገር ግን ሰውነት የሚፈልገውን የውኃ መጠን በአግባቡ ካላገኘ ለዕለታዊ እና በጊዜ ሂደት ሥር ለሚሰድዱ ህመሞች የመጋለጥ ዕድል እንደሚጨምርም ያነሳሉ።

ለመሆኑ ሰውነት የሚፈልገውና በቂ የውኃ መጠን የሚባለው መጠኑ ስንት ነው? በቂ ውኃ አለመጠጣትስ የሚያስከትለው ችግር ምንድን ነው? በሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ላይ የኒውትሬሽን መምህር፣ ተመራማሪ እና ደራሲ ይሁኔ አየለ ምላሽ አላቸው።

አንድ ሰው የሚያስፈልገው የውኃ መጠን በዕድሜ፣ ጾታ፣ በሥራ ባሕርይ፣ በመኖርያ አካባቢ፣ እንደ ጤና ሁኔታው እና እንደ ሰውነት ክብደቱ እንደሚወሰንም በምላሻቸው አስገንዝበዋል።

ለምሳሌ የስኳር ታማሚዎች፣ የምታጠባ እናት፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች፣ ብዙ አድካሚና ላብ የሚያወጡ፣ በሞቃታማ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በቀን 3 ሊትር ውኃ መጠጣት አለባቸው ይላሉ።

በአማካይ ግን በቀን አንድ ሰው ከ2 እስከ 3 ሊትር ውኃ መጠጣት እንደሚጠበቅበት ይገልጻሉ።

ጤናማ ሕይወት የሚመሠረተው ከውኃ ነው፤ ለምሳሌ ውኃማውን 60 በመቶ የሰውነት ክፍል ሚዛን ለማስጠበቅ የግድ አስፈላጊውን መጠን ውኃ መጠጣት እንደሚገባ ይመክራሉ።

በሰውነት ውስጥ የሚካሄደው ሕይወታዊ ሂደት (ባዮሎጂካል ፕሮሰስ) ውኃን መሠረት ያደረገ መሆኑን አስገንዝበው፤ ለምሳሌ ለተስተካከለ የሥርዓተ-ምግብ ሂደት፣ ቆሻሻን ከሰውነት አጣርቶ ለማስወጣት፣ የአጥንት መገጣጠሚያ ሥራን ለማስተካከል እና ለሌሎችም በርካታ የሰውነት ክፍሎች የተሳለጠ ተግባር ውኃ ቁልፍ መሆኑን አንስተዋል።

ይህን ተከትሎም ውኃ ካሎሪ አልባው መድኃኒት (ተፈጥሯዊው መድኃኒት) እስከመባል መድረሱን ነው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ያስረዱት።

ሰውነት የሚያስፈልገውን ያህል ውኃ አለመጠጣት ግን ድካም ያስከትላል፤ ለማየት፣ ለመንቀሳቀስ፣ ለመሥራት፣ ለማሰብ፣ ለመረጋጋት . . . አያስችልምና ሲሉ ያብራራሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንድ ሰው ውኃ የመጠማት መጠኑ ከአራት በመቶ በላይ ከሆነ ለሞት ሊጋለጥ እንደሚችልም ጠቅሰዋል።

ውኃ አለመጠጣት፤ የጨጓራ ህመምን በማባባስ ማስገሳት፣ የቆዳ ድርቀትና ግርጣት፣ የኩላሊት ህመም ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ ያደርጋል ነው ያሉት።

ከምግብ በፊት 30 ደቂቃ ቀድሞ ውኃ መጠጣት ውፍረትን ለመቀነስ እንደሚረዳም ጠቁመዋል።

በቂ ውኃ ከመጠጣት በተጨማሪ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ማዘውተር እንደሚመከርም ገልጸዋል።

የፈላ ውኃ እና የዝናብ ውኃን በብዛት መጠጣት በሰውነት ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድና በኩላሊት ላይም ጫና እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

ለተስተካከለ ጤናማ ሕይወት የግድ ውኃ መጠጣትን ልማድ ማድረግ እንደሚገባም ይመክራሉ።

#ውኃ_መጠጣት #ጤና #ኢዜአ #የኢትዮጵያ_ዜና_አገልግሎት #Ethiopian_News_Agency

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም