ለየጤና ነገር … - ኢዜአ አማርኛ
ለየጤና ነገር …
ስለ ሄርኒያ (ቡዓ) ምን ያህል ግንዛቤ አለዎት? ሄርኒያ ምንድን ነው? መንስዔውስ? በዚህ ጉዳይ ላይ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የሕጻናት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ካሳሁን ግርማ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
• ምንነት
እንደ ዶክተር ካሳሁን ገለጻ፤ ሄርኒያ (ቡዓ) ማለት በሆድ ግድግዳ ላይ ባለ ክፍተት ወይም በሆድ ግድግዳ መሳሳት ምክንያት ሆድ ውስጥ ያሉ የሰውነት ክፍሎች በዋናነት አንጀት ከተፈጥሯዊ ቦታው ሲወጣ ማለት ነው።
በአብዛኛው አዲስ የተወለዱ ሕጻናትን ይይዛል፤ አንዳንድ ጊዜም ቆይቶ ሊከሰት ይችላል የሚሉት ባለሙያው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም እስከ 6 በመቶ የሚወለዱ ወንድ ሕጻናት የሄርኒያ ሰርጀሪ እንደሚያስፈልጋቸው ጥናቶች ያመላክታሉ ብለዋል።
• መንስዔ
መንስዔው እንደታካሚው ዕድሜ ይወሰናል ያሉት ዶክተር ካሳሁን፤ በአጠቃላይ መንስዔዎቹ የሆድ ግድግዳ ክፍተት እና የሆድ ግድግዳ መሳሳት መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በዚህም መሠረት በአብዛኛው ሕጻናት ላይ በዋናነት በተፈጥሮ ያለውን የሆድ ግድግዳ ክፍተት በመጠቀም ዐዋቂዎች ላይ ደግሞ የሆድ ግድግዳ በሚሳሳበት ጊዜ አንጀት አፈትልኮ ከተፈጥሯዊ ቦታ ይወጣል ይላሉ።
• ምልክቶች
ሕጻናት እንደተወለዱ በደንብ በሕክምና ባለሙያ ሊታዩ እንደሚገባ የሚመክሩት ዶክተር ካሳሁን ከሄርኒያ ምልክቶች መካከል፤ በታችኛው የሆድ ክፍል አካባቢ ወይም የዘር ፍሬ ከረጢት የተለየ ዕብጠት መታየት፣ ዕብጠቱ አንዳንድ ጊዜ በራሱ የሚጠፋ ወይም ደግሞ በዕጅ በሚነካበት ጊዜ ወደ ውስጥ የሚገባ ሊሆን ይችላል፣ አንዳንድ ጊዜ ወጥቶ የማይመለስ (ወደ ውስጥ የማይገባ) ዓይነት ዕብጠት ሆኖ የሆድ መነፋት መከሰት እንዲሁም ሀሞት የቀላቀለ ማስመለስ የሚሉት እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
• ሕክምና
ሕክምናው በዋናነት መንስዔውን ማከም መሆኑን አስገንዝበው፤ በዚህም መሠረት መንስዔው የሆድ ግድግዳ ላይ ያለ ክፍተት ወይስ የሆድ ግድግዳ መሳሳት የሚለውን መለየት የሕክምናው አካል መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚያም አንጀት እንዳይወጣ የሆድ ግድግዳ ላይ ያለውን ክፍተት ወይም የሆድ ግድግዳ መሳሳት በቀዶ ሕክምና ማካም እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
በተፈጠረው ክፍተት አንጀት የሚወጣ እና በራሱ የማይመለስ ከሆነ በተለይም በዕጅ በሚነካበት ሠዓት ወደ ሆድ ዕቃ ውስጥ (ወደ ተፈጥሯዊ ቦታው) ካልተመለሰ የአንጀት ደም ዝውውር ስለሚስተጓጎል ጋንግሪን የመሥራት፣ የተሠራጨ ኢንፌክሽን መኖር እንዲሁም እስከ ሞት ሊያደርስ ስለሚችል ለሕክምና ቅድሚያ መስጠትን መክረዋል ባለሙያው።