ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት …

ከየካቲት 29 - መጋቢት 5 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …

✍️ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምሥራቅ ኢትዮጵያ

•  ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድሬዳዋ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል። በዚሁ ወቅትም ድሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተመልክተዋል። ማዕከሉ በውስጡ 10 ተቋማት ይዞ 73 የሚሆኑ አገልግሎቶችን ለዜጎች እየሰጠ መሆኑንም ገልፀዋል።

•  በተመሳሳይ በድሬዳዋ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትን ጎብኝተዋል። ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የአሠራር ሥርዓትን በመከተል ለአምራቾች፣ ለአገልግሎት ሰጪዎች፣ ለላኪዎች፣ ለአስመጪዎች፣ ለተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች፣ ለምርምር ተቋማትና ለሸማቹ ማኅበረሰብ የምርትና አገልግሎቶች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

•  የድሬዳዋ የኮሪደር ልማትንም የጎበኙ ሲሆን፤ የኮሪደር ልማቱ ምቹ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ የተሻሻለ የአካባቢ ውበትን እና ጥራታቸውን የጠበቁ የማኅበረሰብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች በድሬዳዋ ዕውን እንዲሆኑ ማስቻሉን አስረድተዋል።

•  ከድሬዳዋ ነዋሪዎች ጋርም የረመዳን ኢፍጣር መርሐ-ግብር ያከናወኑት ባለፈው ሳምንት ነው።

•  በድሬዳዋ የሚገኘውን እመርታ ቤተ-መጻሕፍትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎብኝተዋል። ቤተ-መጻሕፍቱ በአንድ ጊዜ ለ1 ሺህ ሰው አገልግሎት መስጠት እንደሚችል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

•  በሳምንቱ መጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ ቡርቃ ቀበሌ የተሠራውን የገጠር ኮሪደር ሥራ ተመልክተዋል። የአካባቢው ነዋሪ በንቃት የተሳተፈበት የገጠር ኮሪደር ሥራ፤ ባሕላዊ የግንባታ ዘዴን፣ የተደራጀ ዕቅድ እና ተግባራዊ የአሠራር ውጤት ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

•  የቁንድዶ ተራሮችንም ጎብኝተዋል።

•  በሐረር ከተማ የተቋቋመውን መሶብ የአንድ ማዕከልም ተመልክተዋል። ማዕከሉ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል አቀናጅቶ የማቅረብ ሀገር ዐቀፍ መርሐ-ግብር አካል መሆኑንም አስገንዝበዋል።

•  በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን መልካ በሎ ወረዳ የሚገኘውን ናሲኦል ዋሻም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት ጎብኝተዋል።

•  ከሐረር ከተማ ነዋሪዎች ጋርም የረመዳን ኢፍጣር አካሂደዋል።

✍️ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሹመት መስጠታቸው

•  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ሌ/ጄኔራል አሥራት ደኔሮን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ረዳት ኮሚሽነር ቶፊቅ መደድን እና አቶ ኤርዚቅ ኢሳን የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሮች አድርገው የሾሙት ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

✍️ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው

•  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከልዑካቸው ጋር በጅቡቲ የቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼኽ መሐመድ እና የጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ዑማር ጊሌ በተገኙበት ውይይት አድርገዋል።

•  ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ጉብኝታቸውን ቀጥለውም ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ያቀኑት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። በዚሁ ወቅትም ከፕሬዚዳንት ግርማዊ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ተወያይተዋል።  ውይይታቸውም በሀገራቱ መካከል ለረጅም ዘመናት የቆየውን ወዳጅነት በማጎልበት፤ ትብብር እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነበር።

✍️ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት ጋር መምከራቸው

•  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባዘጋጀው የኢፍጣር መርሐ-ግብር ላይ ታድመዋል። በዚሁ ወቅትም የሁሉም እምነት፣ ባህልና ሥርዓት የሚከበርባት ኢትዮጵያን መገንባት የመደመር መንግሥት ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል።

•  ከዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት ዳይሬክተር ኮስማስ ዛቫዛቫ (ዶ/ር) ጋር በዲጂታል ልማት ያለ ትብብርን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ያደረጉት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ እና ትብብራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በጀመርናቸው እና በሌሎች አዳዲስ ዘርፎች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማምተናል ሲሉም ገልጸዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

•  በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አዘጋጅነት በተከናወነው የኢፍጣር መርሐ-ግብር ላይም የታደሙ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅት “ጎረቤቱ ርቦት እርሱ ጠግቦ የሚያድር ከኛ አይደለም” የሚለው የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) አስተምኅሮ፣ ለሰው ልጅ ክብር መስጠትን፣ ርኅራኄን፣ የጋራ ደስታንና አብሮነትን በተግባር መተርጎም እንዳለብን የሚያሳይ ኅያው የሕይወት ስንቅ ነው ብለዋል።

✍️ የመሬት ናዳና ጎርፍ አደጋ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ

•  ባሳለፍነው ሳምንት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በተከሰተ የመሬት ናዳ እና ጎርፍ የዜጎች ሕይወት አልፏል፤ በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል።

ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች የሐዘን መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

•  ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጋሞ ዞን በመሬት ናዳ አደጋ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ከፌደራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ያስታወቁት ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

እስካሁንም በአደጋው ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስና መልሶ ለማቋቋም ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ በተቀናጀ መንገድ እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ለወገኑ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጁ

•  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ላካ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉትን ዜጎች በማስመልከት ብሔራዊ የሐዘን ቀን ዐውጇል።

በዚህም መሠረት ትናንት የጀመረው ብሔራዊ የሐዘን ቀኑ እስከ ነገ ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

#ባሳለፍነው_ሳምንት #ዐበይት_ጉዳዮች #ኢዜአ #Ethiopian_News_Agency

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም