ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ  22ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሸገር ከተማ ከመቻል ሃዋሳ ከተማ ከባህርዳር ከተማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

በስፔን ጥሎ ማለፍ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል

ከቀኑ 9 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነገሌ አርሲ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች ስድስቱን ሲያሸንፍ፤ በስምንት ተሸንፏል። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 16 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ጎሎችን አስተናግዷል። 

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ24 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ በሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች መካከል 10ሩን ሲያሸንፍ፤ አምስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 22 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 14 ግቦችን አስተናግዷል።

አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ36 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ሁለቱ ቡድኖች ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቻል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ እስከ አሁን 21 ጨዋታዎችን አከናውኖ አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ፤ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 

በ21 ጨዋታዎች ላይ 26 ግቦችን ሲያስቆጥር፤ 27 ግቦችን አስተናግዷል። የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ24 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። 

በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ያሸነፈው መቻል በበኩሉ፤ ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 27 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

መቻል በ31 ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደ ሲሆን፤ ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

የ2016 ዓ.ም የዋንጫ ተፎካካሪ የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሸገር ከተማ ከኢትዮጵያ መድን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ23 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በተመሳሳይ 23 ነጥብ በግብ ክፍያ ብልጫ ወስዶ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሸገር ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ኢትዮጵያ መድን ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከምድረ ገነት ሽሬ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልዋሎ በ21 ነጥብ 19ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ምድረ ገነት ሽሬ በ26 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል።

ምድረ ገነት ሽሬ ተከታታይ የሊግ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። 


 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት እስከ የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ39 ነጥብ እየመራ ነው። 

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ እና የፋሲል ከነማው ታምራት ኢያሱ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር በጋራ እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም