በስፔን ጥሎ ማለፍ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በስፔን ጥሎ ማለፍ ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2018 (ኢዜአ)፦ በስፔን ጥሎ ማለፍ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ በባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ መካከል ዛሬ ይደረጋል።
ጨዋታው ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በካምፕ ኑ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሁለቱ ቡድኖች የካቲት 5 ቀን 2018 ዓ.ም በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ 4 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
አንቶዋን ግሪዝማን፣ ጁሊያን አልቫሬዝ፣ አዲስ ፈራሚው አዴሞላ ሉክማን እና የባርሴሎናው ግብ ጠባቂ ኤሪክ ጋርሺያ በራሱ ላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ውጤቱን ተከትሎ አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቷል።
በአንጻሩ ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገደው ባርሴሎና ውጤቱን የመቀልበስ ከባድ ፈተና ወድቆበታል።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ወደ ፍጻሜ ለማለፍ ከአራት የግብ ልዩነት በላይ ተጋጣሚውን ማሸነፍ ይኖርበታል።
አትሌቲኮ ማድሪድ ማሸነፍ፣ አቻ መውጣት እና ከአራት ጎል ልዩነት በታች መሸነፍ ለፍጻሜ ያሳልፈዋል።
ባርሴሎና የወቅቱ የስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት ነው። 32 ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ ስኬታማው ክለብ ነው።
ተጋጣሚው አትሌቲኮ ማድሪድ የስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫን 10 ጊዜ አሸንፏል።
የ39 ዓመቱ ሪኮርዶ ደ ቡርጎስ ቤንጎትቼአ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።