ቀጥታ፡

በመገጭ ግድብ አዋሳኝ በሆኑ ተፋሰሶች የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራ ማከናወን ተጀመረ

ጎንደር፣ ታኅሣስ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውኃ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ የሚያስችል ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራ ዛሬ ተጀምሯል።

የዘንድሮው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ድባ ደፈጫ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡


 

በዚሁ ወቅት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት፤ የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የመገጭ ግድብ አዋሳኝ በሆኑ 18 ተፋሰሶች ላይ ይካሄዳል። 

በዚህም መሠረት የማሳ እርከንና ክትር ሥራ እንደሚሠራና ሀገር በቀል ችግኞችም እንደሚተከሉ ጠቁመዋል።

የጎንደር ከተማን ሕዝብ የረጅም ዓመታት የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት ታስቦ እየተገነባ ያለውን ግድብ በደለል እንዳይሞላ ከወዲሁ መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አርሶ አደሮች ምርታማነታቸው እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን በውጤታማነት ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

በዞኑ በአንድ ሺህ 52 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው

በአሥተዳደሩ ሥር በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች 847 ሔክታር የሚሸፍን የእርከንና ክትር ሥራ በግድቡ ተፋሰሶች ይከናወናል ያሉት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አበራ አደባ ናቸው፡፡ 

ለአንድ ወር በሚቆየው የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራ ከ8 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል በሕብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራዎች የአፈር ለምነትን በመጨመር የሰብል ምርታማነት እንዲያድግ ማስቻላቸውንም አንስተዋል።

በለሙ ተፋሰሶች በእንስሳት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በወተት ሀብትና በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እየጨመረ መምጣቱንም አመላክተዋል።

በሥራው የተሳተፉ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በአነስተኛ መሬት ብዙ ምርት እንድናገኝና ለእንስሳት በቂ የመኖ እንድናቀርብ አስችሎናል ብለዋል፡፡

የአፈርና ውኃ ዕቀባ ሥራ ምንጮች ጎልብተው መስኖ እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውም ጠቅሰዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም