ቀጥታ፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አርሶ አደሮች ምርታማነታቸው እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ባሕርዳር ፤ ታህሳስ 15/2018 (ኢዜአ)፡ - ባለፉት  ዓመታት  በተከናወነው  የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተጎዳው መሬታቸው አገግሞ  ምርታማነታቸው እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው በባሕርዳር አስተዳደር የዘንዘልማ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናገሩ። 

የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር  የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ዛሬ በዘንዘልማ ቀበሌ በንቅናቄ አስጀምሯል።


 

በማስጀመሪያው መርሃ ግብር  ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

ከተሳታፊ አርሶ አደሮች ውስጥ የዘንዘልማ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ሙላት መኮንን ፤  ለዓመታት  ያከናወንነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የልፋታችንን ዋጋ መልሶ እየከፈለን ነው ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል። 


 

በዚህም ሰብልን ማብቀል ወደ ማቆም ተቃርቦ የነበረው መሬታቸው ለምነቱ እንዲጨምር በማድረጉ የሰብል ምርታማነታቸው እንዲያድግ ብሎም  በቂ የእንስሳት መኖ እንዲያገኙ  ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በማሳቸው አካባቢ  የተከሏቸው የማንጎና ሌሎች የፍራፍሬ ተክሎች ለውጤት በቅተው ተጠቃሚ እንደሆኑ አንስተው፤ዛሬ በተጀመረው ስራ ያለምንም ቀስቃሽ በንቃት መሳተፋቸውንና እንደሚቀጥሉበትም  ገልጸዋል።

አርሶ አደር ደስታው ማንዴ በበኩላቸው፤ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጠልን ያለው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በመጀመሩ ተደስቼያለሁ ብለዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በተከናወነው ስራ ምርታማነታቸው ማደጉን ገልጸው፤  ያገኘሁትን ጥቅም ለማሳደግም ዛሬ በተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ያለማንም ቀስቃሽ  ወጥተን እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ በተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ በጥራትና በውጤታማነት ተምሳሌት እንዲሆን አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሰሉ ብርሃኑ ናቸው።


 

ባለፉት ዓመታት የተራቆቱ አካባቢዎችን በመለየት የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በመሰራቱና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በመደረጉ የአየር ንብረቱ እንዲስተካከልና የዝናብ መጠኑ እየጨመረ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በሚለሙ ተፋሰሶች ላይ አርሶ አደሩ የፍራፍሬና የመኖ ችግኞችን እንዲተክል በማድረግ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።


 

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ፤ የዘንድሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ስራ በአስተዳደሩ ስር በሚገኙ በ12 የገጠር ቀበሌዎች በጥራት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በተለዩ ተፋሰሶች ከ1ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ዛሬ የተጀመረው ተግባር በቀጣይ ለ30 ቀናት   እንደሚቆይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም