ቀጥታ፡

በዞኑ በአንድ ሺህ 52 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ታህሳስ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው የበጋ ወራት በአንድ ሺህ 52 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ።።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ባለሙያ አቶ ጤናው አላምረው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአፈር እና የውሃ ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነትን ጠብቆ በማቆየት ለሰብል ምርታማነት ማደግ የጎላ ሚና እያበረከተ ነው።

እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ተመናምኖ የቆየውን የደን ሃብት መልሶ በመተካት የደን ሽፋኑ ከፍ እንዲል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዚህ የበጋ ወራት በ1 ሺህ 52 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል።

በተፋሰሶቹ ከ83 ሺህ 700 ሄክታር በላይ ለምነቱን ያጣ መሬት የሚሸፍን የልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራው ከታህሳስ 1/2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ሲሆን ለዚሁ የሚሆን የስራ መሳሪያ እና 39 ሺህ ቀያሽ አርሶ አደሮችን በማሰልጠን እንዲሳተፉ እየተደረገ ይገኛል። 

እስካሁን ስራ በተጀመረባቸው አካባቢዎችም ከአንድ ሺህ 800 ሄክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።

የጥራት ደረጃውን ለማስጠበቅና ዘላቂነቱን ለማረጋገጥም በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች ሙያዊ እገዛና ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ አስረድተዋል።

በአዋበል ወረዳ የጎደና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይመኑ መንግስቱ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የተከናወነበት ማሳ ለምነቱ በመሻሻሉ በሰብል ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል።

ባገኙት ውጤት በመበረታታትም በዚህ የበጋ ወቅት በልማት ቡድን በመደራጀት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን እያከናወኑ እንደሚገኝም ገልፀዋል። 

በዞኑ ባለፈው ዓመት 56 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደተከናወነ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም