ቀጥታ፡

በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን በውጤታማነት ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

ባሕርዳር፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን በውጤታማነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ሰው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተመላከተ።

‎የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ በዘንዘልማ ቀበሌ ዛሬ ተጀምሯል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሰሉ ብርሃኑ እንዳሉት፤ የተጎዳ አካባቢን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን በውጤታማነት ማጠናከር ያስፈልጋል።

ከተያዘው ወር መግቢያ ጀምሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በተለዩ ተፋሰሶች የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ ቀበሌ የተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ ጣናን ከደለል የሚታደግ እንደሆነም ገልጸዋል።

‎በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተጀመረው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራን በውጤታማነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ሰው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አመልክተዋል።

‎የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው፤ ከዛሬ ጀምሮ ለ30 ቀናት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው በ12 ቀበሌዎች በተለዩ 24 ተፋሰሶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

‎የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራው ጥራቱን በጠበቀና ዘላቂነት ባለው መልኩ በማከናወን ወደ ጣና ኃይቅ የሚገባውን ደለል መከላከል በሚያስችል አግባብ እንዲከናወን ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በዘንዘልማ ቀበሌ በተጀመረው የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ መርሃ ግብር የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም