በአረንጓዴ ዐሻራ ጸንቶና ተግቶ መሥራት ዘመኑ የሚፈልገው ዐርበኝነት - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ ዐሻራ ጸንቶና ተግቶ መሥራት ዘመኑ የሚፈልገው ዐርበኝነት
በዮሐንስ ደርበው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በቢሾፍቱ አስጀምረዋል።
መርሐ-ግብሩ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትና ብልጽግና አሠናሥሎ የሚያረጋግጥ ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም በዚሁ ወቅት በአጽንዖት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የደን፣ የሰብልና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ወሳኝ የልማት አቅጣጫም ነው።
ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለተከላ ዝግጁ በሆኑበት በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ ወቅት፤ አረንጓዴ ለሆነች ነገ፣ ሁላችንም ተስፋን እንትከል ሲሉም ለሀገሬው ጥሪ አቅርበዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ - ለዓየር ንብረት ለውጥ ላለመበገር የሚደረግ ትጋት
• ከችግኝ ተከላ ያለፈ ድርብርብ ጥቅም ያለው ኢኒሼቲቭ
የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ለሀገር በቀል ችግኞች፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ላላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ለውበት የሚሆኑ ዛፎች፣ የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ ያሚያስችሉ እና የደን ሽፋንን በማሳደግ ለከባቢ አየር መስተካከል ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ያሉ ችግኞች የሚተከሉበት ነው።
በዚህ ሁሉ ሂደት የአፈር መሸርሸርና መከላት ቀንሷል፣ የጎርፍ አደጋዎች ቀንሰዋል፣ የብዝኃ ሕይወት መመናመን ቀንሷል፣ የመሬት መራቆት ቀንሷል፣ የውኃ አካላት በደለል መሞላትና መጥፋት ቀንሷል፤ በአንጻሩ ምርትና ምርታማነት ጨምሯል።
ነገ ከዚህ የበለጠ ውጤት እንዲገኝ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን የሕዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጠው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በነቂስ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ከተጀመረ ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ከሀገራዊ ለውጡ በፊት 17 ነጥብ 2 በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን አሁን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል።
በሕዝቡ ዘንድ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ተፈጥሮን የመንከባከብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ ጭምር ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።
ይህ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሙ በተጨባጭ እየተገለጠ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል።
#ተስፋን_እንትከል #ኢዜአ #አረንጓዴ_ዐሻራ