ቀጥታ፡

ባሳለፍነው ሳምንት …

በዮሐንስ ደርበው

ከግንቦት 2 እስከ ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከተከናወኑ ዐበይት ጉዳዮች መካከል …
 
· ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ጋር መምከራቸው
 
ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂየቫ ጋር መክረዋል። በዚሁ ወቅትም በኢኮኖሚያዊ እድገት፣ በአጋርነት እና ቅድሚያ በሚሰጣቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ‎ለነበረን ጠቃሚ የሐሳብ ልውውጥና ቀጣይነት ላለው አጋርነትም ምስጋናዬ የላቀ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
 
· ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ፎርዋርድ ጉባዔ
 
በኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እና በፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጋራ አዘጋጅነት በናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ፎርዋርድ ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ተሞክሮ አካፍለዋል።
 
በዚሁ ወቅትም በተለይም የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ልማት እና የኃይል ሽግግርን በተመለከተው ውይይት ላይ ከተሞክሯችን የተቀዱ ከፍ ያሉ ሐሳቦች ተነስተዋል ብለዋል። አክለውም፤ ኢትዮጵያ በተነሱት ሁለት ዘርፎች የጀመረችውን ሥራ በማጠናከር የላቀ ሚና መጫወቷን ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።
 
· የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ
 
ባሳለፍነው ሳምንት የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን፤ በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንኳን ደህና መጡ ስል ሁልጊዜም በልዩ ኩራትና ደስታ ነው ሲሉ ተቀብለዋቸዋል።
 
ከአቀባበሉ በኋላም፤ መሪዎች በጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። በዚህም መሠረት፤ በታዳሽ፣ የተቀናጀ እና ዘላቂ ኃይል እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን ፕሮግራምን ለመተግበር የሚውል የ54 ነጥብ 6 ሚሊየን ዩሮ ብድርን ጨምሮ የ150 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል የመንግሥትና የግል አጋርነት አዲስ የማዕቀፍ እና የፍኖተ ካርታ ስምምነት ተፈርሟል።
 
· ‎ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞ
 
‎ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ፣ "በሰላም አብሮ ለመኖር" በሚል መሪ ቃል ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ ማውጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ አድርገዋል።
 
‎እነዚህ አራት ቴምብሮች እ.ኤ.አ. በ1945 በሳን ፍራንሲስኮ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተርን ከመፈረም ጀምሮ፤ በኮንጎ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን እስከማሰማራት እና በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እስከ ማስተናገድ ያለውን የጋራ ታሪካችንን የሚተርኩ ናቸው ብለዋል።
 
በዓለም የፖስታ ኅብረት በኩል ለ192 ሀገራት የተሰራጩት እነዚህ ቴምብሮች፤ ለአንድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ለትውልድ ሁሉ የሚተርፍ የታሪክ ዐሻራ ማሳያ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
 
‎በተያያያዘም፤ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና ለቡድናቸው፣ በዘመናዊው ታሪክ ውስጥ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ ሰላምን፣ ልማትን እና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር እያሳዩት ላለው ጽኑ አመራር ጥልቅ አድናቆታችንን እንገልጻለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
‎የተባበሩት መንግሥታት የጸናው ሀገራት ከመከፋፈል ይልቅ ውይይትን ስለመረጡ መሆኑን አስገንዝበው፤ ‎ኢትዮጵያም ይህንኑ የሁልጊዜ ምርጫዋን ታጸናለች ሲሉ አረጋግጠዋል።
 
· የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ባሳለፍነው ሳምንት ተካሂዷል።
 
በዚሁ ወቅትም የምክክር ባህል እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው፤ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበረሰብ ባህል ግንባታ ደግሞ ያላሰለሰ የመነጋገር ልምምድ እና የሰከነ የወል መደማመጥን ግድ ይላል ብለዋል።
 
የእስካሁን ሂደቱም በማኅበረሰባችን በየደረጃው የመደማመጥን ከፍ ያለ ጠቀሜታ አሳይቷል ሲሉም ገልጸዋል።
 
ሂደቱ በሀገራችን ሁሉም ማዕዘናት የሚገኙ ከ90 በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያንን አመለካከቶች እና የውይይት ውጤቶች ያንፀባረቀ ሆኗልም ነው ያሉት።
 
ለሀገር ወሳኝ ፋይዳ የያዘው የምክክሩ ምዕራፍ ተጨባጭ ውጤት ወደሚያስገኘው ቀጣይ ምዕራፍ በሚሸጋገርበት በዚህ ወቅት፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለሀገራችን ሰላም፣ አንድነት እና ዘላቂ መረጋጋትን የሚያረጋግጥ የጋራ ፅኑ አቋም እና ገንቢ በሆነ መንገድ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
 
· የገላን ኢንዱስትሪ ፓርክ መመረቅ

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክን በመረቁበት ወቅት፤ ፓርኩ አስተማማኝ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ተደማሪ እመርታ ነው ብለዋል።

ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ የንግድ ከባቢ ከመፍጠር ባሻገር በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶቻችን የሥራ ዕድል ይከፍታል ሲሉም ገልፀዋል።

‎ፓርኩ የሀገራችን አምራቾች አቅማቸውን በማጎልበት፣ ምርታማነታቸውን ማሳደግና ተወዳዳሪነታቸውን በመጨመር ለከተማችን፣ ለሀገራችንና ለቀጣናው የሚተርፉበት ታላቅ እድልን ይዟል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ተኪ ምርቶችን በማምረት በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ቀጥተኛና ቀልጣፋ የንግድ ትስስር ይፈጥራል፤ ምርቶችን ደግሞ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉ አስረድተዋል።

· ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባዔ መጀመር 

 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባሳለፍነው ሳምንት ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ጉባዔን ባስጀመሩበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ለልማት በምታደርገው ቆራጥ ጥረት ውስጥ የሰው ተኮር የልማት አቅጣጫ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዋና ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አስገንዝበዋል። በዚህም መሠረት መንግሥት መጪው ትውልድ ጤናማ፣ ብቁ እና ውጤታማ እንዲሆን የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ማዕከል በማድረግ ሁሉን አቀፍ ሥራ እየተገበረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
 
በመላ ሀገሪቱ ከ35 ሺህ በላይ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት የነጻና አስገዳጅ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን እያደረግን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ልጆች ላይ መሥራት በነገ ሀገር ላይ መሥራት በመሆኑ ተባብረን፣ በጊዜ የለንም መንፈስና በትጋት እንሥራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
 
· የፖሊሲ ቀን
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት፤ ባሳላፍነው ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያው የፖሊሲ ቀን ተከብሯል። በዚሁ ወቅትም፤ ውጤታማ ፖሊሲ ለሀገራዊ ዕድገት የጀርባ አጥንት መሆኑን አስገንዝበው፤ መንግሥት በግልፅ፣ ተተግባሪና ጥራት ባላቸው ፖሊሲዎቹ ለሕዝብ የገባውን ቃል እየተገበረ ስኬትም እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
 
ሀገራችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በምትገኝበት በዚህ ወቅት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በጂኦ-ፖለቲካዊና በቴክኖሎጂ ለውጦች ላይ ቀድሞ ምላሽ የሚሰጡ ጥናቶች ያስፈልጋሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት በዕውቀት ላይ ኢንቨስት በማድረግ እና ለማስረጃዎች ዋጋ በመስጠት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነ የፖሊሲ ሥነ-ምኅዳር ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። ለዚህ ስኬት ሁላችንም በጋራ እንሥራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም