ለረጅም ሠዓታት የሚቀመጡ(የሚቆሙ) ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄ - ኢዜአ አማርኛ
ለረጅም ሠዓታት የሚቀመጡ(የሚቆሙ) ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄ
በዮሐንስ ደርበው
የጤና ነገር . . .
ከሥራ ባሕርያቸው እንዲሁም ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ለረጅም ሠዓታት የሚቀመጡ እና የሚቆሙ ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረጉ ለጤና ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ።
ተከፍሎ የማያልቅ የኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ውለታ አለብን - የመናዊያን ፍልሰተኞች
በሣይንስ የታወቁ (የሚመከሩ) ጤናማ እና ጤናማ ያልሆኑ አቀማመጦች እንዳሉ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የአጥንት ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት፣ የመገጣጠሚያ ቅየራ እና የአርትሮስኮፒ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት ዶክተር ሰኢድ መሐመድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከሥራ ባሕርያቸው ጋር በተያያዘ ለረጅም ሠዓታት የሚቀመጡ (የሚቆሙ) ሰዎች ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ አብራርተዋል።
👉 እንቅስቃሴ ሳያደርጉ በአንድ ቦታ ለረጂም ጊዜ አዘውትሮ መቀመጥ (መቆም)
• ሣይንስ በአንድ ቦታ ከ30 እስከ 45 ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜ መቀመጥን እንደሚመክር ዶክተር ሰኢድ ይናገራሉ።
• የእንቅስቃሴ ለውጥ አስፈላጊነትን የሚገልጹት የሕክምና ባለሙያው፤ እንደ ሥራ ባሕርያቱ ከ45 ደቂቃ በላይ መቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በመሐል እየተነሱ ከ 3 እስከ 4 ደቂቃ ሰውነትን ማፍታትና መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
👉 እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ለረጂም ጊዜ አዘውትሮ መቀመጥ ያሚያስከትለው ጉዳት
• ለጤናማ የሰውነት እንቅስቃሴ ሰውነትን ማፍታታት ወሳኝ መሆኑን እና በአንድ ቦታ ለረጅም ሠዓት መቀመጥ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአማካይ በ45 ደቂቃ አንድ ጊዜ ለ4 ደቂቃ ሰውነትን ማፍታት እንደሚገባ የሕክምና ባለሙያው መክረዋል።
እንቅስቃሴ ሳይኖረው ለረጂም ሠዓት መቀመጥን ማዘውተርና እንቅስቃሴ የራቀው ሰውነት፤ ለደም መርጋት፣ ስኳር፣ ደም ግፊት እንዲሁም ለልብ ህመም እና መሰል በሽታዎች የመጋለጥ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ያስረዳሉ።
• በተጨማሪም ለረጂም ሠዓት በአንድ ቦታ መቀመጥ (መቆም) ከአጥንት ጋር የተያያዘ ጉዳት ያስከትላል ብለዋል። በተለይም መቀመጫ፣ ዳሌ እና ብሽሽት አካባቢ ያሉ ጡንቻዎች በጊዜ ሂደት ጥንካሬያቸውን እንዲያጡና እንዲላሉ ያደርጋል ሲሉ ለአብነት አንስተዋል።
• ይህን ተከትሎም ቀልጣፋና በቀላሉ የሚታዘዝ ሰውነት እንዳይኖር ያደርጋል ያሉት ዶ/ር ሰኢድ፤ ለምሳሌ፡- ከተቀመጥንበት እንድንነሳ የሚያደርጉን ጡንቻዎች በሂደት ጥንካሬ የማነስ እና የሰውነት መክበድ (ለመነሳት ሲሞክሩ ሰውነቴ ከበደኝ የማለት ስሜት)፣ ለመነሳትና ለመቀመጥ ብሎም ለመንቀሳቀስ መቸገርን ያስከትላል ብለዋል።
• እንዲሁም እግርን ደራርቦ (አንዱን እግር በሌላኛው ላይ አድርጎ) መቀመጥ የዳሌ መዛነፍን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶችን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።
• በአጠቃላይ በመሐል እንቅስቃሴ የሌለው ረጂም ሠዓት መቀመጥ፤ የዳሌ መገጣጠሚያ እንደ ልብ እንዳይታጠፍና እንዳይዘረጋ በማድረግ ጉዳት ያመጣል ነው ያሉት።
• ወደ ኋላም ሆነ ወደ ፊት እንዲሁም ወደ ጎን ከመንጋደድ በመቆጠብ ቀና (ቀጥ) ብሎ መቀመጥ እንደሚገባ መክረዋል።
ይህም ከመገጣጠሚያ እና አጥንት ጋር የተያያዙ የአንገት ሥር፣ ማጅራት እና ጀርባ ህመምን መቀነስ እንደሚያስችል አስረድተዋል። በተጨማሪም ያለ ዕድሜ መጉበጥን ለመከላከል ይረዳል ነው ያሉት።