በሻምፒዮንስ ሊጉ ባየር ሙኒክ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ድል ቀንቷቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሻምፒዮንስ ሊጉ ባየር ሙኒክ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጥሎ ማለፍ ሶስት ጨዋታዎች ተደርገዋል።
በቤርጋሞ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ባየር ሙኒክ አተላንታን 6 ለ 1 ረትቷል።
ማይክል ኦሊሴ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ጀማል ሙሲያላ፣ ኒኮላስ ጃክሰን፣ ሰርጌ ናብሪ እና ጆሲፕ ስታኒሲች ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ማሪዮ ፓሳሊች ለአተላንታ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
በጨዋታው ባየር ሙኒክ ፍጹም የበላይነት ወስዷል።
የጀርመኑ ኃያል ክለብ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ እድሉ እጅጉን የሰፋ ሆኗል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አትሌቲኮ ማድሪድ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 5 ለ 2 አሸንፏል።
በዋንዳ ሜትሮፓሊታኖ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ጁሊያን አልቫሬዝ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አንቶዋን ግሪዝማን፣ ማርኮስ ሊዮሬንቴ እና ሮቢን ለኖርማንድ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል።
ፔድሮ ፖሮ እና ዶምኒክ ሶላንኬ ለቶተንሃም ጎሎቹን ከመረብ ጋር አገናኝተዋል።
በጨዋታው አትሌቲኮ ማድሪድ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል።
በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቶተንሃም ደካማ እንቅስቃሴ አሳይቷል።
የማድሪዱ ክለብ ወደ ሩብ ፍጻሜ የማለፍ እድሉን አስፍቷል።
በሴንት ጀምስ ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኒውካስል ዩናይትድ እና ባርሴሎና አንድ አቻ ተለያይተዋል።
ሃርቪ ባርንስ በ86ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ኒውካስትልን መሪ አድርጓል።
ጨዋታው በኒውካስትል አሸናፊነት ተጠናቀቀ ሲባል ላሚን ያማል በ96ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ለባርሴሎና የአቻነቷን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ እና አዝናኝ ፉክክር ተደርጎበታል።
ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ ጨዋታ ጋላታሳራይ ሊቨርፑልን 1 ለ 0 አሸንፏል።
የመልስ ጨዋታዎች በቀጣይ ሳምንት ይካሄዳሉ።