ቀጥታ፡

ሐዋሳ ከተማ ወሳኝ ድል አሳክቷል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ሐዋሳ ከተማ መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፏል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ፤ አምበሉ ሽመልስ በቀለ በ75ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ከሶስት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ሐዋሳ ከተማ በ40 ነጥብ ደረጃውን ከሶስተኛ ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል።

ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ማድረግ ችሏል። በውድድር ዓመቱም 11ኛ ድሉን አስመዝግቧል።

በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቀሌ 70 እንደርታ በ22 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።



 

በሌላኛው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ናይጄሪያዊው ጄሮም ፍሊፕ እና አብዱልራህማን መሐመድ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በሊጉ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ በ19 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃ ይዟል። ላለመውረድ በሚያደርገው ፉክክር ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

በውድድር ዓመቱ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አዳማ ከተማ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ 23ኛ ሳምንት ተጠናቋል።

የ24ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከመጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም