በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ባየር ሙኒክ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ባየር ሙኒክ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን አሸነፈ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፡- በጀርመን ቡንድስሊጋ የ24ኛ ሳምንት ተጠባቂ መርሐ-ግብር ባየር ሙኒክ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 3 ለ 2 አሸንፏል።
ማምሻውን በሲግናል ኢዱና ፓርክ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሃሪ ኬን በጨዋታ እና በፍጹም ቅጣት ምት ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ጆሹዋ ኪሚች ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ኪሚች በ87ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ግቧን አስቆጥሯል።
ኒኮ ሽሎተርቤክ እና ዳንኤል ስቬንሰን የዶርትሙንድን ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ባየር ሙኒክ ሁለት ጊዜ ተመርቶ ጨዋታውን አሸንፏል።
"Der Klassiker" የደርቢ ጨዋታ በባየርን የበላይነት ተጠናቋል።
ሃሪ ኬን የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል። በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ወደ 30 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት መሪነቱን አጠናክሯል።
በሊጉ 20ኛ ድሉን ያስመዘገበው ባየር ሙኒክ በ63 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ከተከታዩ ዶርትሙንድ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 11 ከፍ አድርጓል።
በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በ52 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።