ቀጥታ፡

በዞኑ የለሙ ተፋሰሶች በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን አሳድገውልናል-ተጠቃሚዎች 

አርባ ምንጭ ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- በጋሞ ዞን የለሙ ተፋሰሶች ምርትና ምርታማነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ አኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደጉን በዞኑ የሚገኙ ተጠቃሚዎች ገለፁ።

በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ እየተከናወነ ነው

ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ወደ ትርፍ ምርት- የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት

በዞኑ በበጀት ዓመቱ ወደ 160 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት እየተከናወነ መሆኑም ተመላክቷል።

ተጠቃሚዎቹ እንደገለፁት፤ በዞኑ የለሙ ተፋሰሶች ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭ ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን አሳድጎልናል ብለዋል።

አርሶ አደር ሚሊዮን በየነ በዞኑ የቁጫ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፤ በአካባቢያቸው ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የተጎዳ መሬት ሲያገግም፣ የጠፋ ምንጭ ዳግም ሲፈልቅ እና የአካባቢው ስነ-ምህዳር ወደ ልምላሜ ሲቀየር በዓይናቸው ተመልክተዋል።

አመቺ ባለመሆናቸው ለእርሻ ስራ ጥቅም ላይ ሳይውሉ የቆዩ የእርሻ ማሳዎች ጥቅም ላይ ውለው ወደ ምርታማነት ተቀይረው ሲመለከቱ ደግሞ እውን ሳይሆን ህልም መስሏቸውም ያውቃል። 

አሁን ላይ በተፋሰስ ልማት ስራው በለማው መሬት ላይም በእንስሳት እርባታና በንብ ማነብ ስራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።


 

ለውጡንም በማየታቸው በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን ብቻም ሳይሆን ቤተሰባቸውንም በማስተባበር እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአርባ ምንጭ ከተማ የ"ነህሚያ የእንስሳት እርባታ ማህበር" ሰብሳቢ ወጣት ህዝቅኤል ኦሎባ የማህበሩ አባላት የተፋሰስ ልማቱ በፈጠረላቸው ጸጋ ተነሳስተው ባለፈው ዓመት በሦስት ላሞች እና በሁለት ኮርማዎች ሥራ መጀመራቸውን አስታውሷል።

በተፋሰሱ በለማው ቦታ ላይም መንግስት ባመቻቸላቸው ብድር ለእንስሳት መኖ በማምረት ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መሆኑንም ጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅት ከላሞቹ አምስት ጥጃዎችን ማግኘታቸውን የጠቀሰው ወጣቱ ለተለያዩ አካላት የወተት ምርት በማቅረብ የገቢ ምንጫቸው ማደጉን አስረድቷል፡፡

በአካባቢው የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ጥሩ የስራ ዕድል ይዞልን መጥቷል ያለው ደግሞ በዞኑ ምዕራብ አባያ ወረዳ በአንኮበር ቀበሌ "የጦይሎ ንብ አንቢዎች ማህበር" ሰብሳቢ ወጣት አለማየሁ ቶጋ ነው።

ማህበሩ በ2014 ዓ.ም እንደተመሰረተ የሚናገረው አለማየሁ በለማው ተፋሰስ ላይ በአንድ በኩል ንብ እያነቡ በሌላ በኩል የለማው ከባቢ እንዳይጎዳ ጥበቃ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብሏል።

መንግስት 30 ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን፣ አንድ የማር ማጣሪያ ማሽንና መስሪያ አልባሳት እንዳበረከተላቸው ገልጾ አስፈላጊው የሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አልሸሸገም።

''በዓመት ከ3 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ማር እየሸጥን ራሳችንን ከመቻል ባለፈም ቤተሰቦቻችንን እያገዝን እንገኛለን'' ብሏል።


 

የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቅነህ ካልሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የተፋሰስ ልማት በተለያየ መልክ የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

የተጎዳ መሬትን እንዲያገግም በማድረግ ብሎም ስነ-ምህዳርን በማስተካከል ምርትና ምርታማነት እንዲረጋገጥ በማስቻል የአርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በተያያዘ የነዋሪዎች ግንዛቤ እየሰፋ በመምጣቱ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ተዳምሮ ምርት በስፋት እየተመረተ ይገኛል ብለዋል።

በያዝነው በጀት ዓመትም በ336 ንዑስ ተፋሰሶች 160 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አቶ ወርቅነህ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም