ቀጥታ፡

ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ወደ ትርፍ ምርት- የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት

ደሴና ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-  ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ወደ ትርፍ ምርት-የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት

በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ እየተከናወነ ነው

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን እያሳደገ መሆኑን አርሶ አደሮች ይመሰክራሉ።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተከለቻቸው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የአፈር ለምነትን በመመለስና የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን ከአርሶ አደሩ ባለፈ የተለያያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በመርሃ-ግብሩ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች ቀደም ሲል ተራቁቶ የነበረን መሬት እንዲያገግም አድርገዋል።


 

ደርቀው የነበሩ ምንጮች እንዲፈልቁና የወንዞች የውሃ መጠን እንዲጨምር በማድረግም ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።

ይህም በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ይገኝ የነበረውን 7 ኩንታል ምርት ወደ 20 ኩንታል አሳድጓል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምስራቅ ጎጃምና የደቡብ ወሎ ዞን አርሶ አደሮችም በአረንጓዴ አሻራ የታገዘው የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ ምርታማነታቸውን በእጥፍ ማሳደጉን ይናገራሉ።


 

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ የሽንቡሪ ቀበሌ አርሶ አደር በቃሉ ፈቃድ እንደሚሉት፣ ቀደም ሲል በእርሻ ማሳቸው ላይ ይገጥማቸው የነበረው የአፈር መሸርሸር ለምርታማነት መቀነስ ዋነኛ ምክንያት ነበር።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ያከናወኑት የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ የእርሻ ማሳቸውን ለምነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል። 

ከ10 ዓመት በፊት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ያገኙት የነበረው ምርት ከ7 ኩንታል በታች እንደነበር አስታውሰው፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመታገዝ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ በመስራታቸው አሁን ላይ ከ20 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ አመልክተዋል።

ይህ ውጤት በዘንድሮው በጋ እየተካሄደ በሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ላይ ያለማንም ቀስቃሽ በቁርጠኝነት ለመሳተፍ መነሳሳትን እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለውሃ ሀብት መጨመር ምክንያት ሆኗል። 

በምስራቅ ጎጃም ዞን የጎዛምን ወረዳ  አርሶ አደር በእድሉ ጫኔ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ባከናወኗቸው የተፈጥሩ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች የከርሰ ምድር ውሃ መጨመሩንና ደርቀው የነበሩ ምንጮች መፍለቃቸውን አመልክተዋል።

ይህም ለመስኖ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራ ላይ በመሰማራት ተጨማሪ ገቢ እንዳገኝ አድርጓል ብለዋል።


 

በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተመሳሳይ ስኬቶች እየተመዘገቡ ነው። 

አርሶ አደር ሱለይማን መሀመድ እና ያስን መሀመድ እንደተናገሩት፣ በአረንጓዴ አሻራ የተሰሩ እርከኖችና ክትሮች የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ በማድረጋቸው በየሄክታሩ ከ2 እስከ 3 ኩንታል የምርት ጭማሪ አግኝተዋል።


 

የወል መሬቶችን በማልማትም በቆላ ፍራፍሬና በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ እድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን የግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ቡድን መሪ ንጉሴ ሽመልስ እንደገለጹት፣ በዘንድሮው በጋ ከአንድ ሺህ በላይ ተፋሰሶች ላይ 84 ሺህ ሄክታር መሬትን የሚሸፍን የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን ከ50 በመቶ በላይ ተከናውኗል።


 

በተመሳሳይም የደቡብ ወሎ ዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊ አህመድ ጋሎ፣ በዞኑ በ58 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንና እስካሁን ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ መከናወኑን ገልጸዋል። 


 

አርሶ አደሩ በዘርፉ እያገኘ ያለው ተጨባጭ ጥቅም ለስራው ስኬታማነት ትልቁን ድርሻ እየተወጣ  መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም