በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ እየተከናወነ ነው
አዳማ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በበጋ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ እንዳሉት፤ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ ከጥር አጋማሽ ጀምሮ በህዝብ ተሳትፎ በሁሉም መዋቅሮች እየተካሄደ ይገኛል።
ልማቱ እየተከናወነ ያለው በዞኑ በ11 ወረዳዎች ከ119 ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም የተለያዩ የአፈርና የድንጋይ እርከኖች፣ የእርጥበት ማቆያዎች፣ የክትር ሥራዎች፣ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮች ስራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ለጉዳት የተጋለጠ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የመከለል ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራውን ለማቀላጠፍ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረው ልማቱ በሚከናወንባቸው ቦታዎችም የችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተሰራው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት አካባቢው ልምላሜና ነፋሻማ አየር መላበሱን ጠቅሰው የአፈር መሸርሸር ቀንሶ እርጥበት በመጨመሩ ምርትና ምርታማነት ማደጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች የግብርናና የእንስሳት ምርትና ምርታማነት መጨመሩን፣ የከርሰ ምድር ውሃ መጎልበቱንና ለመስኖና ለጓሮ አትክልት ልማት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አቶ አብነት አስረድተዋል።
በዞኑ የቦሰት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጉተማ ቢፍቱ በወረዳው እየተካሄደ ባለው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ በርካታ አርሶ አደሮች፣ የወጣቶች እና የሴቶች አደረጃጀቶች በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በበጋው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ የማሳና የጋራ ላይ እርከን፣ የውሃ ማፋሰሻና መቀልበሻ ቦዮች እንዲሁም የተለያዩ የውሃ ማስረጊያ ስትራክቸሮች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም የአፈር ለምነት እንዲሻሻልና ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ በተፋሰሶቹ በዘላቂነት የእንስሳት መኖ ለማግኘት እና ልቅ ግጦሽን ለመከላከል ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ከመለወጡም በተጨማሪ ከሰውና እንስሳ በተከለሉ መሬቶች ላይ አርሶ አደሩ የእንስሳት መኖን እያገኘ መሆኑን ጠቁመዋል።