ወላይታ ድቻ እና ባህርዳር ከተማ በሊጉ ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ድል አስመዘገቡ - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻ እና ባህርዳር ከተማ በሊጉ ወደ አሸናፊነት የተመለሱበትን ድል አስመዘገቡ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሐ-ግብር ዛሬ በ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ይጀመራል
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲዳማ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ወላይታ ድቻ ከ2 ለ 0 መመራት ተነስቶ መቻልን 4 ለ 3 አሸንፏል።
ዮናታን ኤልያስ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ቴዎድሮስ ኃይለማርያም እና ካርሎስ ዳምጠው ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ለመቻል ቸርነት ጉግሳ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በረከት ደስታ ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል።
ከዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ወላይታ ድቻ በ19 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በሊጉ ስድስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቻል በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
በሌላ መርሐ-ግብር ባህርዳር ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል። በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ግርማ ዲሳሳ በ36ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
ከአምስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል መንገድ የተመለሰው ባህርዳር ከተማ ደረጃውን ከዘጠነኛ ወደ ሰባተኛ ከፍ አድርጓል። በሊጉ አምስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በውድድር ዓመቱ ስምንተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በ24 ነጥብ ከነበረበት 10ኛ ደረጃ ወደ 11ኛ ዝቅ ብሏል።