በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲዳማ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲዳማ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14 /2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሐ-ግብር ዛሬ በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኟው ዙር ጅማሮ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ይጀመራል
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሲዳማ ቡና በዳሳሽ ሰውአገኝ ጎል ቦሌ ክፍለ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በውድድር ዓመቱ አምስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና በ18 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
በአንጻሩ በሊጉ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቦሌ ክፍለ ከተማ በ23 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አማሩ አብተው እና አለሚ በዬቻ የማሸነፊያ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሄለን እሸቱ ለልደታ ክፍለ ከተማ ብቸኛውን ግብ አስቆጥራለች።
በሊጉ ሁለተኛ ድሉን ያስመዘገበው አዲስ አበባ ከተማ በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃ ይዟል።
በውድድር ዓመቱ 10ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ልደታ ክፍለ ከተማ በበኩሉ በተመሳሳይ ስምንት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ይርጋጨፌ ቡና እና አርባምንጭ ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መታሰቢያ ክፍሌ ለይርጋጨፌ ቡና ፣ ስንዱ ዳምጠው ለአርባምንጭ ከተማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። አርባምንጭ ከተማ በዘጠኝ ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።