ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ ዛሬ በ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ይመለሳል።

በዕለቱ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በዚህም መሠረት ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፋሲል ከነማ ምሽት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ21 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። ፋሲል ከነማ በ33 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም።

ቡድኖቹ በመጀመሪያው ዙር በመጀመሪያ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ምሽት 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ20 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። አዳማ ከተማ በ28 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

መድን ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ወላይታ ድቻ ከመቻል ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ወላይታ ድቻ በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። መቻል በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ወላይታ ድቻ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ተጋጣሚው መቻል ማሸነፍ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ ያደርገዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሀዲያ ሆሳዕና ከባህርዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና በ24 ነጥብ 10ኛ፣ ባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ 24 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ያላሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና እና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ባህርዳር ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ 3 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።



የ20ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና በ20ኛ ሳምንት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ እንዲሸጋገር መደረጉን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

ሲዳማ ቡና በ35 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው በተመሳሳይ አምስት ግቦችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም