የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት የሚጥል ነው
ደሴ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡-ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል መሆኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የአካል ጉዳተኞችን የፈጠራ አቅም በማጎልበት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ታዳጊዎች ለፈጠራና ለክህሎት እንዲጠቀሙበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል
ኢትዮጵያ የበለጸገ ኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን በምታደርገው ጥረት ውስጥ ቴክኖሎጂ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
የሀገሪቷን የ5 ዓመት የቴክኖሎጂ ልማት ጉዞ የሚመራበት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል።
የስትራቴጂው ትግበራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት በማፋጠን ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የወሎ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ያነሳሉ።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራ በዋናነት የመንግስት አገልግሎቶችን በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርን በመከላከልና ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሀዋ ወሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በየዘርፉ የተጀመሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራሮች ሥራን ከማቅለልና አገልግሎትን ከማቀላጠፍ ባለፈ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ቴክኖሎጂን የማስፋፋት፣ የማላመድና የጥናትና ምርምር ስራዎችን በትኩረት የማከናወን ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን እንዲታጠቁ በማድረግ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሥራ እድሎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የኢንፎርሜሽን ሲስተም መምህር ታደሰ ቢራራ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ ለዘርፉ የሰጠችው ትኩረት በ2030 የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
በቴሌ ብር፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና በ"ኢትዮ ኮደርስ" ስልጠናዎች የታየው ስኬት አገልግሎትን ከማቀላጠፍ ባለፈ ብልሹ አሰራርን መከላከልና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እያስቻለ ነው ብለዋል።
ግብርናን፣ ቱሪዝምንና ንግድን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር መቻሉ ለሀገሪቷ ሁለንተናዊ እድገት መፋጠን መሰረት የሚጥል መሆኑንም ነው ያብራሩት።
በገጠር አካባቢዎች የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ማስፋትና አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂን የተላመደ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራትና የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።