ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ታዳጊዎች ለፈጠራና ለክህሎት እንዲጠቀሙበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ታዳጊዎች ለፈጠራና ለክህሎት እንዲጠቀሙበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይገባል
አዳማ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የዲጂታል ቴክኖሎጂንና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) ታዳጊዎች ለፈጠራና ለክህሎት ማጎልበቻ እንዲጠቀሙበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ ተገለጸ።
ለታዳጊዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የበየነ-መረብና ሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ተደራሽ ማድረግን ያለመ የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል ።
ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች ከዘመኑ ጋር አብረው እንዲራመዱና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን እንዲያበረክቱ በዲጂታሉ አለም እውቀት እንዲያካብቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መብራት ባጫ፤ የወደፊቷ አገር የምትገነባው በሀገር ተረካቢዎች ፈጠራ እና ክህሎት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ታዳጊዎች ስልኮቻቸውንና ኮምፒውተሮቻቸውን ለጨዋታ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ለዲጂታል ፈጠራዎች እንዲያውሏቸው የማድረግ ሃላፊነት አለብን ብለዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂንና ሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) ታዳጊዎች ለፈጠራና ለክህሎት ማጎልበቻ እንዲጠቀሙበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ አፅዕኖት ሰጥተዋል።
ለዚህም በተለይም ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶችና የወጣቶች ማእከላት ትልቅ ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው ለነገዋ ብሩህ ኢትዮጵያ ዛሬ ልጆችና ታዳጊዎች ላይ እንስራ ሲሉ ተናግረዋል።
የታዳጊዎችና ህፃናትን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ጨምሮ በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዲጂታል ትግበራና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የትምህርትና የፈጠራ ማእከላትን በማስፋፋት በዘርፉ የተማረና የተመራመረ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።