ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን የፈጠራ አቅም በማጎልበት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

ወላይታ ሶዶ ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የአካል ጉዳተኞችን የፈጠራ አቅም በማጎልበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ "አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት" በሚል መሪ ሃሳብ 34ኛውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለያዩ ኹነቶች እያከበረ ይገኛል።


 

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ካሰች ኤልያስ በወቅቱ እንዳሉት፤ የአካል ጉዳተኞች አካታችነትን በማጠናከር ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል።

በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ አሉታዊ አመለካከቶችን በማስወገድ አቅማቸውን እንዲያወጡ የተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ውጤት ማሳየቱንም ጠቁመዋል።

በዚህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ እንዲሁም ድምፃቸው እንዲሰማ አርአያ ለሆኑ አካል ጉዳተኞች ዕውቅና የመስጠት እንዲሁም ተሞክሮአቸውን የማሸጋገር ተግባር ይጠናከራል ብለዋል።


 

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ፤ አካል ጉዳተኞች አስፈላጊው ድጋፍ ከተደረገላቸው የፈጠራ አቅማቸውን በማውጣት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል።


 

በክልሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች በርካታ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን በማንሳት እምቅ አቅማቸውን እንዲያወጡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ፤ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን የፈጠራ እና የትምህርት ዕውቀት ለማውጣት ያለውን የአመለካከት ችግር ማረም ይገባል ብለዋል።


 

የለውጡ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች የሰጠው ልዩ ትኩረት ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ማድረጉንም ጠቁመዋል::

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ደነቀ ዳጮ፤ በክልሉ የአካል ጉዳተኞችን ሰብዓዊ መብት በማስከበር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለውጥ አምጪ ፕሮግራሞችን በመቅረጽና ተሳትፏቸውን በማሳደግ አካል ጉዳተኞችን ሊደግፉ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በመድረኩ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም