ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በተጠባቂው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ

ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋሩ

ከመርሐ-ግብሮቹ መካከል ሲዳማ ቡና ከባህርዳር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው ስድስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 23 ግቦችን ሲያስቆጥር 9 ጎሎችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በ33 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

በሊጉ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች መካከል አራቱን ያሸነፈው ባህርዳር ከተማ በበኩሉ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በ10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦች ተቆጥረውበታል።

ባህርዳር ከተማ በ22 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ በሊጉ ለበርካታ ጊዜ አቻ የወጣ ቡድን ነው።

ሲዳማ ቡና በ17ኛ ሳምንት በነገሌ አርሲ ካስተናገደው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ድል ከቀናው ከተከታዩ ሐዋሳ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ነጥብ ከፍ ያደርጋል።

በሌላ በኩል ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ መቻል ከሸገር ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቻል በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች በስምንቱ ድል ሲቀናው አራት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 23 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 13 ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ29 ነጥብ ሶስተኛ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በበኩሉ በሊጉ 17 ጨዋታዎችን በማድረግ ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ በስድስቱ ተሸንፏል። ስምንት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ17 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፈው መቻል በድል ጉዞው ለመቀጠል ይፋለማል። ካሸነፈ በድጋሚ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ይመለሳል።

በአንጻሩ ባለፉት ስምንት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ሸገር ከተማ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና በመጠኑም ቢሆን የሚርቅበትን እድል ይሰጠዋል።

እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ሲይዝ ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 20 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለፉት ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በ17ኛ ሳምንት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሽንፈት ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም