በተጠባቂው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በተጠባቂው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ተባረክ ሄፋሞ በ49ኛው እና ጌታነህ ከበደ በ93ኛው ደቂቃ ላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በውድድር ዓመቱ ዘጠነኛ ድሉን ያስመዘገበው ሃዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ ከነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ወደ ሁለተኛ ከፍ ብሏል። ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ አንድ ዝቅ
አድርጓል።
በአንጻሩ በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ26 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ምድረ ገነት ሽሬ እና ኢትዮጵያ መድን ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ምድረ ገነት ሽሬ በ22 ነጥብ 10ኛ፣ ኢትዮጵያ መድን በ19 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዘዋል።
ምድረ ገነት ሽሬ ባለፉት የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል ርቋል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ የተጀመረው የወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።