ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከነገሌ አርሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 19 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል። 

ከመርሐ-ግብሮቹ መካከል ነገሌ አርሲ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚገነባው ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

መቻል ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ

አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በውድድር ዓመቱ 16 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሰባቱ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በአምስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።  

17 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ 12 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ነገሌ አርሲ በ26 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 16 ጨዋታዎች ዘጠኙን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪው ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 23 ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዷል። 

ሲዳማ ቡና በ33 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። 

ነገሌ አርሲ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።  

በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ ባካሄዳቸው 16 ጨዋታዎች አምስቱን አሸንፎ በሰባቱ ተሸንፎ አራት ጊዜ አቻ ተለያይቷል።14 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ19  ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው 16 ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን በድል ሲወጣ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። በስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በ16ቱ ጨዋታዎች ላይ 19 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 20 ጎሎች ገብተውበታል። 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ17 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻሉም። 

ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሸገር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ16 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ድሬዳዋ ከተማ በ19 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። 

ሸገር ከተማ ባለፉት ሰባት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም