መቻል ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
መቻል ኢትዮጵያ መድንን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር መቻል ኢትዮጵያ መድንን 1 ለ 0 አሸንፏል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቸርነት ጉግሳ በ43ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው መቻል በ29 ነጥብ ደረጃውን ከአምስተኛ ወደ ሁለተኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ ስምንተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ ሰባተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን በ18 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ26 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ወላይታ ድቻ በ15 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ባለፉት ሰባት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።
ቀን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ምድረ ገነት ሽሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።