በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚገነባው ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሚገነባው ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ
ወላይታ ሶዶ፣ ጥር 18/2018(ኢዜአ)-፡-በወላይታ ሶዶ ከተማ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለሚገነባው ስታዲየም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ናቸው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት የለውጡ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታችው ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
የአካባቢው ስፖርተኞች በሀገራዊና በዓለም መድኮች ጎልተው እንዲታዩ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት ስታዲየሙ በታቀደለት ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ በቅርበት በመከታተል ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው የስቴዲየሙ መገንባት የስፖርት ዘርፉን ለማጠናከር ካለው ፋይዳ ባለፈ የህብረተሰቡን እንድነት ያጠናክራል ብለዋል።
ስታዲየሙ በ51 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍና 40ሺህ ተመልካቾችን እንደሚያስተናግድ ጠቁመው ለግንባታው ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።