ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ክብር አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተኝተን አናድርም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን ክብር፣ አንድነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተኝተን አናድርም ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርኢት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኢትዮጵያን ለመድፈር ለሞከሩ ኃይሎች ሁነኛ መድሃኒት ሆኖ ሀገር ያጸና ተቋም ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ማደግ ከቻለች የጸናች እና የተከበረች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንችላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት 90 ዓመታት በብዙ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ አልፏል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የ85 ዓመቱን ስራችንን የሚተካከሉ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይል፣ አየር በአየር፣ አየር በምድር ብቻ ሳይሆን ከአየር ጥቃት ኢትዮጵያን ለመከላከል የሚያስችሉ አቅም መገንባቱን ጠቅሰዋል።

በአየር ኃይል መብቃት፣ ማሳደግ የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት በስጋና በአጥንት ድል ማስመዝገብ ያደረ፣ የቀረ ስርዓት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተኩስ አቅም፣ በቴክኖሎጂ ብዙ ምሽጎች ማፍረስና ውጊያን ማሳጠር ታሳቢ ያደረገ አቅጣጫ እንከተላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አሁን ያለውን የአየር ኃይል አቅም በእጥፍ ደረጃ ለማሳደግ ግልጽ እቅድ፣ በጀት እና ምንጭ ለይቶ ከዋና ዋና አምራቾች ጋር በትብብር ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በ2030 ወደ አምስተኛው ትውልድ የሚሸጋገር፣ በቁጥርም ከተዋጊም አኳያ አሁን ያለው በእጥፍ እንደሚያድግ ገልጸዋል።

ጠላቶቻችን ከቅርብና ከሩቅ የኢትዮጵያን አጠቃላይ አቅም ለማዳከም፣ ስትራቴጂክ ጥቅሞቿን ለማደናቀፍና ጥቅሞቿን ለመጋራት በብዙ ደክመዋል፣ በብዙ ሰርተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከወዳጆቿ ጋር በትብብር ለመስራት በሯ ክፍት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በትብብር አብሮ ለመስራት፣ አብሮ ለማደግ ያለንን ቁርጠኝነት አረጋግጣለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያን ክብር፣ አንድነትና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተኝተን የማናድር መሆኑን በድጋሚ አረጋግጣሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ካለችበት የታሪክና የሀብት ጥልቀት በተጨማሪ አሁን ላይ በዘመናዊ የጦር ቴክኖሎጂ ራሷን እያዘመነች መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም በድሮው አስተሳሰብና ቴክኖሎጂ ላይ ለቀሩ አካላት የኢትዮጵያን እድገትና ወደፊት መራመድ በቅጡ ሊረዱት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ጋር ተስማምቶና ተባብሮ ማደግ ብቸኛው አዋጭ መንገድ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ትናንትና ላይ የቆመች ሀገር አይደለችም ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም