ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ማደግ ከቻለች የጸናች እና የተከበረች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንችላለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፦‎ኢትዮጵያ በሚዛን በሁሉም ዘርፍ ማደግ ከቻለች የጸናች እና የተከበረች ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ እንችላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ አመት ክብረ በዓል እየተከናወነ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በክበረ በዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90 ዓመት ቢሆንም ለረጅም ዓመታት በቂ እና ተከታታይ ግንባታ እንዳልተደረገለት ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት 85 ዓመቱን የሚተካከል የኢትዮጵያ አየር ኃይል በቴክኖሎጂ፣በሰው ኃይል እና ኢትዮጵያን ከአየር ጥቃት መከላከል የሚያስችል ብቃት መገንባቱን አመልክተዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አሁን ያለንበትን የአየር ኃይል አቅም በእጥፍ ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዛሬ የአራተኛውን ትውልድ የመዋጋት አቅም የገነባው አየር ኃይሉ እ.አ.አ በ2030 ወደ አምስተኛው ትውልድ እንዲሸጋገር ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በወታደራዊ አቅም ብቻ የተሟላ እድገት ማምጣት እንደማትችል እና ሁሉን አቀፍ እድገት እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል።

በኢኮኖሚ፣በዲፕሎማሲ፣ፖለቲካ እና ወታደራዊ በሚዛን ሁሉን ማሳደግ ስንችል የጸናች ፣ የተፈራች እና የተከበረች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማስረከብ እንችላለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከወዳጆቿ ጋር ለመስራት ሁሉም በሯ ክፍት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለጠላቶቻችን መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም፣አንድነት እና ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አንተኛም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብልጽግና እና እድገት የማረጋገጥ ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ይህንን የሚያቆም የትኛውም ኃይል እንደሌለ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ትናንት ላይ ቆማ የቀረች ሀገር አይደለችም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ነገን የዋጀ አቅም መገንባቷን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም፣አንድነት እና ብልጽግና በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር እውን ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለሁሉ የምትበቃ እና ለሁሉም የምትሆን ለማድረግ በትጋት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም