ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኢትዮጵያን ለመድፈር ለሞከሩ ኃይሎች ሁነኛ መድሃኒት ሆኖ ሀገር ያጸና ተቋም ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኢትዮጵያን ለመድፈር ለሞከሩ ኃይሎች ሁነኛ መድሃኒት ሆኖ ሀገር ያጸና ተቋም ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የጥቁር አንበሳ የአየር ላይ ትርኢት እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አየር ኃይሉ ባለፉት 90 ዓመታት በብዙ ከፍታና ዝቅታ ውስጥ አልፏል።

አየር ኃይሉ ኢትዮጵያን በየትኛውም አቅጣጫ ለመድፈር ለሞከሩ ኃይሎች ሁነኛ መድሃኒት ሆኖ ሀገር ያጸና ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ባለፈ በቅኝ ግዛት ማብቂያ ዘመን የታንዛኒያን አየር ክልል የጠበቀ የአፍሪካዊያን ኩራት መሆኑንም አንስተዋል።

አየር ኃይሉ አሁን ላይ በዘመናዊ ትጥቅ እየታገዘ በላቀ ብቃት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

እኛ ያለ ኢትዮጵያ እናት የለንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ እናታችን መተኪያ የሌላት መሆኗን በመገንዘብ ለሀገር ልዕልና በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይልን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አሁን ካለው አቅም በእጥፍ ለማሳደግም ከወዲሁ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተያዘው በጀት ዓመት የ10 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንደምታስመዘግብ ያለፉት ስድስት ወራት አፈጻጸም ማመለከቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ይህ ዕድገት ሙሉ የሚሆነው ጠንካራ ወታደራዊና ጸጥታ ተቋማትን በመገንባት ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ትናንት ላይ የቆመች ሀገር አይደለችም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አየር ኃይሏ ነገን የዋጀ እንዲሁም ዘመኑ የደረሰበትን አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እኛ የሰው አንፈልግም፣የራሳችንንም አንሰጥም፤የተሰጠብን ካለም ማወራረዳችን አይቀርም ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም