ቀጥታ፡

በክልሉ የዳበሩ የግጭት መፍቻ ስርዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው-ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የዳበሩ የግጭት መፍቻና የፍትሕ ስርዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።

በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትብብር “የሕግ የበላይነትና አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች - ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

ከትናንት በጎ ዕሴቶችን መውሰድ፤ዛሬ ጠቃሚ አዳዲስ ዕሴቶችን መገንባት፤ ነገ ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚያደርጓት ቁልፍ ተግባራት ናቸው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

በክልሉ የፍትሕ ተቋማትን ተምሳሌትና የልምድ ተሞክሮ መቅሰሚያ የሚያደርጉ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያሉ የዳበሩ የግጭት መፍቻና የፍትሕ ሥርዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

በኮንፍረንሱ የተነሱት የህግ የበላይነት፣ አማራጭ የልዩነት መፍቻ መንገዶች፣ የዘላቂ ሰላምና የዘላቂ ልማት አጀንዳዎች አንገብጋቢና ወቅታዊ ናቸው ብለዋል።

በሀገራችን ከለውጡ ወዲህ ከአጀንዳዎች ሁሉ ከፍ ብሎ የመጣው የመልማትና ሁለንተናዊ የብልፅግና አጀንዳ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ኢትዮጵያን በታሪክ ከምትጠቀስባቸው የግጭትና የድህነት አዙሪት አላቅቆ የበለፀገችና ለሌሎች ምሳሌ የሆነች ሀገር ለመገንባት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ የልማት አጀንዳ በተቀሰቀሰበት በዚህ ወቅት በንግግር ሊፈቱ የሚችሉ ጉዳዮችን በኃይል ለማስፈጸም የሚሞክሩ አካላት የህብረተሰቡን ሰላም የሚነሱና የመልማት ፍላጎት የሚገቱ ችግሮችን መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

ልማት ሰላም ይፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የለውጡ መንግሥት ስለ ሰላም የዕይታና የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ ዘላቂ ሰላምን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አካሄድን ቀዳሚ አማራጭ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የማንግባባባቸው ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ መዘርጋቱን አንስተው፥ መንግሥት ሁልጊዜም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ ባለው ፅኑ አቋም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን ማድረጉን አስረድተዋል።

በአማራ ክልል የሰላም አማራጭን መርጠው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የተመለሱ አካላት ለዘላቂ ሰላም ግንባታው ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና የልማት ሥራዎች መሳካት ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በመሆኑም የታሪክና የትውልድ ተጠያቂነትን ከሚያስከትል ጥፋት በመቆጠብ መንግሥት ለሰላም የሰጠውን ዕድል በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም በጎ ሚና መጫወት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከሰባ በላይ አማራጭ ባህላዊ የግጭትና የችግር መፍቻ ስርዓቶች መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ በአማራ ክልልም ለባህላዊ ስርዓቶች የተሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የዳበሩ የግጭት መፍቻና የፍትሔ ስርዓቶችን በአግባቡ መጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም