በክልሉ የፍትሕ ተቋማትን ተምሳሌትና የልምድ ተሞክሮ መቅሰሚያ የሚያደርጉ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፍትሕ ተቋማትን ተምሳሌትና የልምድ ተሞክሮ መቅሰሚያ የሚያደርጉ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የፍትሕ ተቋማትን ተምሳሌትና የልምድ ተሞክሮ መቅሰሚያ የሚያደርጉ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተዘጋጀው “የሕግ የበላይነትና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች -ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ እንደገለጹት፤ በክልሉ ግጭቶች የሚፈቱበት የዳበረ ባህላዊ እሴት መኖሩን ጠቅሰል፡፡
ይህንን ሀብት ተቋማዊ ለማድረግ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የክልሉን የዳኝነትና የፍትሕ ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ለማድረግ የሚያስችሉ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ነጻ፣ገለልተኛ፣ጠንካራና ተጠያቂነት ያለው የዳኝነት ሥርዓት ለመገንባት የክልሉ መንግሥት ጠንካራ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለዚህም ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የፍርድ ቤቶችን ተቋማዊ ነጻነት የሚያጠናክሩ የሕግ ማሻሻያዎች ተደርገው በክልሉ ምክር ቤት ጸድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው በበኩላቸው፤ የዳኝነት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን አብራርተዋል።
ፍርድ ቤቱ የጀመረውን የዲጂታላይዜሽን ፕሮግራም ተከትሎም ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው መዝገብ ማስከፈትና አቤቱታ ማቅረብ የሚችሉበት ኢ-ፋይሊንግ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች በአካል ሳይገኙ በቴክኖሎጂ ታግዘው ክርክር የሚያደርጉበት የርቀት ክርክር (Remote Litigation) አሠራር መተግበሩን ጠቅሰው፥ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ደረጃ የተደራጁ ዘመናዊ ችሎቶች በስፋት ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ የአፍሪካ ሕብረትን ወክለው የተገኙት አምባሳደር ሳሌህ መሐመድ፤ መድረኩ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን የመልካም አስተዳደርና የመረጋጋት አጀንዳ ለማራመድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በመድረኩ ያለው ተሳትፎ ሂደቱን ለመደገፍ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ የፍትሕ ሪፎርም ተሞክሮ ለመቅሰም ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል።