ከትናንት በጎ ዕሴቶችን መውሰድ፤ዛሬ ጠቃሚ አዳዲስ ዕሴቶችን መገንባት፤ ነገ ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚያደርጓት ቁልፍ ተግባራት ናቸው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ከትናንት በጎ ዕሴቶችን መውሰድ፤ዛሬ ጠቃሚ አዳዲስ ዕሴቶችን መገንባት፤ ነገ ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚያደርጓት ቁልፍ ተግባራት ናቸው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ጥር 16/2018(ኢዜአ)፦ከትናንት በጎ ዕሴቶችን መውሰድ፤ዛሬ ጠቃሚ አዳዲስ ዕሴቶችን መገንባት፤ ነገ ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚያደርጓት ቁልፍ ተግባራት ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር "የሕግ የበላይነትና አማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች - ለዘላቂ ሰላም እና ዕድገት" በሚል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ ጉባኤን አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ መደበኛ የፍርድ ተቋማቷን ብታዘምንም አብዛኛው ሕዝባችን ችግሩን የሚፈታበት ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓት ግን ተገቢው ቦታ ሳይሰጠው ቆይቷል ብለዋል፡፡
አሁን ግን በሀገራችንም ሆነ በክልላችን ተደራሽ፣ ቅቡልነት ያለው እና በመርሕ ላይ የቆመ ፍትሕን ለማስፈን እንዲቻል መደበኛና ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ተጣጥመውና ተናብበው የሚጓዙበትን ዐውድ መፍጠር የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
ለዚህ ደግሞ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶቻችንን ከዘመናዊ ዕሳቤዎች ጋር ማስተሣሠር፣ በሕግ መደገፍ እና አሠራሮቻቸውን ማዘመን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከምንተገብራቸው ሪፎርሞች ጋር አሠናስሎ ማዋወቀር ለነገ የማይባል ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጎደላቸውን ሞልተን በትክክል ከተጠቀምንባቸው፣ በጉዳዮች ብዛት በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙ መደበኛ የፍትሕ ተቋሞቻችንን ትርጉም ባለው ደረጃ ያግዛሉ፤ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሻለ ተቀባይነት እና የባለቤትነት ስሜት የሚንጸባረቅባቸውን መፍትሔዎች ያቀርባሉ።
ይህ ኮንፈረንስ ይሄንን አዎንታዊ ጥምረት ለመፍጠር የተሻለውን መንገድ እንደሚጠቁም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡