ሀገራዊ ሪፎርሙ ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ሪፎርሙ ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል
አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ሀገራዊ ሪፎርሙ ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) " የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ" ኮንፈረንስ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ ሪፎርሙ ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለትውልድ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመፍጠርና ያሉትን በማዘመን ጠንካራ መሠረት እየገነባች ነው
ማንኛውም ተግባራዊ ሥራ ሰው የመፍጠር አቅም እንዳለው ተናግረው፤ እያንዳንዱ ቀን ትምህርት ነው፤እያንዳንዱ ፈተና ደግሞ ለትምህርት ግብዓት ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን እንደ ዕድል በመጠቀም መማርና ማደግ እንደሚቻልም ተናግረዋል።
የሪፎርሙ ውጤትና የአመራር ብቃት ሪፎርሙ ሲጀመር የነበሩ አመራሮች በሂደቱ እውቀታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጋቸውን ጠቁመው፤ እንደአዲስ ወደ አመራር የመጡት ደግሞ ኢትዮጵያ ተስፋና መሪዎች እንዳሏት ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ማለት ሁሉንም አውቀን አልጨረስንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁንም ብዙ የሚቀሩ የቤት ሥራዎች አሉ ብለዋል።
የገንዘብ ምንዛሬ ተመን ውሳኔ ወቅት የነበረውን ሁኔታ በምሳሌነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፥ በወቅቱ ውሳኔ ለማሳለፍ ለሁለትና ሦስት ዓመታት ሰፊ ክርክሮች፣ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
ከተሳካላቸው ሀገራት ልምድ መቀሰሙን አመልክተው፤ ያልተሳካላቸው ሀገራትን ደግሞ በጥልቀት በማጥናት ትምህርት መቀሰሙን ተናግረዋል።
ይህ የጥናትና የክርክር ሂደት በአመራሩ ውስጥ ከፍተኛ የራስ መተማመን፣ልምድ እና እውቀት መፍጠሩን ጠቅሰው፤አሁን እየታየ ያለው ውጤት የሂደቱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የሀገር ሀብት አጠቃቀም ግልጽነት፣ ተጠያቂነት እና ተገማችነት ባለው መንገድ መመራት እንዳለበት ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገሪቱን ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደር ቴክኖሎጂን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።