የሀገርን ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት የኢንቨስትመንት ተዋናዮች ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት የኢንቨስትመንት ተዋናዮች ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2018(ኢዜአ)፦ የሀገርን ብልጽግና በማረጋገጥ ሂደት የኢንቨስትመንት ተዋናዮች ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ" ኮንFረንስ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በመደመር ዕሳቤ መሰረት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሚናቸው ተለክቶና ታውቆ በዚያው ልክ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
የግሉን ዘርፍ የሚያቀጭጭ እንቅስቃሴ መከተል አዳዲስ ፈጠራዎችን ያጠፋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፈጠራ መቀዛቀዝ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለሀገር ዕድገት ትልቅ እንቅፋት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
በመሆኑም መንግሥት የግሉ ዘርፍና አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች(ስታርታፖች) እንዲጠናከሩ አመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ እንደ አፈር ማዳበሪያና ኢነርጂ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መልክ መያዛቸው ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የፈጠረውን ዕድል በማሳያነት ጠቅሰው፤ በልማቱ ግራና ቀኝ ባሉ እንደ ሞል፣ ሬስቶራንትና ሌሎችም ንግዶች አማካኝነት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ብር ገደማ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም ትልቅ እመርታ እንዲያመጡ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለዚህም እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማት እያስመዘገቡት ያለው ስኬት ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።
ዳያስፖራው በሀገሩ የልማት ጉዳይ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን መንግሥት የጀመረውን የማበረታቻ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።