ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለትውልድ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመፍጠርና ያሉትን በማዘመን ጠንካራ መሠረት እየገነባች ነው

አዲስ አበባ፤ጥር 9/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለትውልድ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመፍጠርና ያሉትን በማዘመን የኢኮኖሚ ፍላጎትና የሕዝብ ብዛት መሸከም የሚችል ጠንካራ መሠረት እየገነባች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ" በሚል በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ተቋማትን የማደራጀት ጉዳይ መነሻው ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሊያሳካ የሚፈልጋቸውን ግቦች ውጤታማ ለማድረግ የተቋማት ግንባታ ዋነኛው መሣሪያ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥሩ ሐሳብ በተቋማት ታግዞ ወደ ተግባር ካልተለወጠ ትርጉም አልባ ነው ብለዋል፡፡

የተቋም ግንባታ ሐሳቦች ከግለሰቦች አልፈው ለብዙኃን እንዲደርሱ የሚያስችል የለውጥ ምሰሶ መሆኑን አስረድተዋል።

ውጤታማ ተቋም በሕግና በሥርዓት የሚመራ፣ ለተገልጋዮቹ የታመነ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው እንዲሁም ለወደፊት መቀጠል የሚያስችል ጽኑ መሠረት የያዘ መሆን ይኖርበታልም ብለዋል። 

የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለመለወጥ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ አጀንዳ ሲቀረጽ ነባር ተቋማትን የማዘመን ተግባር መከናወኑን አመልክተው፤ ሌሎችን ደግሞ አዲስ በማዋቀር ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም እንደ ኢትዮጵያ ያለ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር የካፒታል ገበያ እንዳልነበራት በማሳያነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ አዳዲስ አሠራሮችና አመራሮች ይዘው የመጡ ተቋማት በርካታ ለውጦችን እያስመዘገቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ እየዘመነች ባለችበት ሂደት ውስጥ መሰል ተቋማት ካልተገነቡ፣ ሐሳቦችን ተሻግሮ ለትውልድ ማድረስና ውጤት ማምጣት እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።

ያሉትን ተቋማት ማዘመንና የጎደሉትን መሙላት ዘመኑን በሚዋጅ አግባብ መሥራት ሕልም ካለው ሀገርና ኩባንያ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ ለትውልድ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመፍጠርና ያሉትን በማዘመን፣ የሀገሪቷን የኢኮኖሚ ፍላጎትና የሕዝብ ብዛት መሸከም የሚችል ጠንካራ መሠረት እየገነባች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም