በአፍሪካ ዋንጫ ግብጽ እና ናይጄሪያ ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ግብጽ እና ናይጄሪያ ሶስተኛ ደረጃን ለማግኘት ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ ዛሬ በግብጽ እና ናይጄሪያ መካከል ይደረጋል።
ጨዋታው ምሽት አንድ ሰዓት ላይ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይካሄዳል።
በግማሽ ፍጻሜው ግብጽ በሴኔጋል፣ ናይጄሪያ በሞሮኮ ሽንፈት አስተናግደዋል።
የዓለም አይኖች ያረፉበት ተጠባቂው የማንችስተር ደርቢ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታል
ግብጽ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ እስከ አሁን ባደረገቻቸው ስድስት ጨዋታዎች አራቱን ስታሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፋለች። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይታለች።
በጨዋታዎቹ ላይ ስምንት ግቦችን ስታስቆጥር አምስት ጎሎችን አስተናግዳለች።
ተጋጣሚዋ ናይጄሪያ ከስድስት ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ስታሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፋለች። 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ አራት ጎሎች ተቆጥሮባታል።
ናይጄሪያው በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ግቦችን ያስቆጠረች ሀገር ናት።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለ10ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ናይጄሪያ በአምስቱ ድል ሲቀናት ግብጽ ሁለት ጊዜ አሸንፋለች። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በጨዋታዎቹ ላይ ሁለቱም ሀገራት በተመሳሳይ 11 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ሀገራቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአህጉራዊው መድረክ የተገናኙት ጋና እ.አ.አ በ1963 ባዘጋጀችው አራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ነው።
በወቅቱ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ግብጽ 6 ለ 3 አሸንፋለች።
ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ካሜሮን እ.አ.አ በ2022 ባስተናገደችው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው።
በምድብ አራት ባደረጉት ጨዋታ ናይጄሪያ በኬሌቺ ኢናቺዮ ግብ ግብጽን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ናይጄሪያ የአፍሪካ ዋንጫን ሶስት ጊዜ ስታሸነፍ ግብጽ ሰባት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የውድድሩ ስኬታማ ሀገር ናት።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኃያላን የሆኑት ሁለቱ ሀገራት በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ባይደርሱም ሶስተኛ ደረጃን ይዞ በአዎንታዊ መልኩ ውድድሩን ለማጠናቀቅ ይፋለማሉ።
የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ነገ በሴኔጋል እና አዘጋጇ ሞሮኮ መካከል ይደረጋል።