የዓለም አይኖች ያረፉበት ተጠባቂው የማንችስተር ደርቢ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አይኖች ያረፉበት ተጠባቂው የማንችስተር ደርቢ
አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ22ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ማንችስተር ዩናይትድ በ32 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንችስተር ሲቲ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ198ኛ ጊዜ ነው።
ቡድኖቹ ከዚህ በፊት ባደረጓቸው 197 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 80 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 63 ጊዜ ሲያሸንፍ 54 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ 57 ጊዜ ተገናኝተው ማንችስተር ዩናይትድ 26 ጊዜ ሲያሸንፍ ሲቲ በ21ዱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ ሶስቱን ሲያሸንፍ ማንችስተር ዩናይትድ አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ የአንድ ከተማ ባላንጣ ቡድኖች ናቸው።
ክለቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1881 ነበር። በዚህ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ 3 ለ 0 አሸንፏል።
ቡድኖቹ ከመጀመሪያ ጨዋታቸው አንስቶ ለ145 ዓመታት የቆየ ፉክክር በእንግሊዝ እና በአውሮፓ መድረክ አድርገዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉን ዋንጫ 20 ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 10 ጊዜ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
ማንችስተር ዩናይትድ በጊዜያዊ አሰልጣኙ ማይክል ካሪክ እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል።
ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ 3 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ክለቦቹ በተመሳሳይ ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
የ47 ዓመቱ የማንችስተር ከተማ ተወላጅ አንቶኒ ቴይለር ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
በሌላ በኩል የሊጉ መሪ አርሰናል ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ከኖቲንግሃም ፎረስት ጋር በሲቲ ግራውንድ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
ሊቨርፑል ከበርንሌይ፣ ቼልሲ ከብሬንትፎርድ፣ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከዌስትሃም ዩናይትድ፣ ሰንደርላንድ ከክሪስታል ፓላስ እና ሊድስ ዩናይትድ ከፉልሃም በተመሳሳይ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።