ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2018 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15 ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማ ከሲዳማ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አዳማ ከተማ በሊጉ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ በአምስቱ ድል ሲቀናው በሁለቱ ተሸንፏል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ 22 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

ሲዳማ ቡና በሊጉ ካከናወናቸው 14 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ሲያሸንፍ የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 18 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ሊጉን 29 ነጥብ እየመራ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች 14 ሳምንት አቻ ከተለያዩባቸው መርሐ-ግብሮች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። አዳማ ከተማ ከሁለት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።

በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 14 ጨዋታዎች ላይ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።

ኢትዮጵያ ቡና 18 ነጥብ 11 ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ 14 ጨዋታዎች ሰባቱን አሸንፎ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዶ በሶስቱ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ሃዋሳ ከተማ 24 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሁለቱም ቡድኖች በአሸናፊነት ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ 19 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ድሬዳዋ ከተማ 18 ነጥብ 12 ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከመቻል በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

አርባምንጭ ከተማ በስምንት ነጥብ የመጨረሻውን 20 ደረጃን ይዟል። መቻል 20 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ ያላሸነፈ ብቸኛው ክለብ ነው። መቻል ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።

ጨዋታው አርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ፣ መቻል ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም