ቀጥታ፡

የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር ከቡርኪናፋሶ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው  

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜ የሚያልፉ ቀሪ ሁለት ሀገራት የሚለዩባቸው ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ። 


 

የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ኮትዲቯር ከቡርኪናፋሶ ጋር ምሽት አራት ሰዓት ላይ በማራካሽ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ኮትዲቯር በምድብ ስድስት በሰባት ነጥብ አንደኛ በመያዝ 16 ውስጥ ገብታለች።

ተጋጣሚዋ ቡርኪናፋሶ በምድብ አምስት በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፍ መግባቷን አረጋግጣለች።

ግብጽ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች

ናይጄሪያ ለሩብ ፍጻሜ አለፈች

ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

አንጎላ እ.አ.አ በ2010 ባዘጋጀችው 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ጋቦን እ.አ.አ በ2012 በጣምራ ባዘጋጁት 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተመሳሳይ በምድብ ሁለት ባደረጉት ጨዋታ ኮትዲቯር 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ሰለሞን ካሉ እና የቡርኪናፋሶው የቀድሞ ተጫዋች ባካሪ ኮኔ በራሱ ላይ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ኮትዲቯር የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ናት። 

ቡርኪናፋሶ ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ2013 ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሳ በናይጄሪያ 1 ለ 0 የተሸፈችበት ውጤት በአህጉራዊ መድረኩ ምርጡ ውጤቷ ነው።

ኮትዲቯር የአፍሪካ ዋንጫ ክብሯን የማስጠበቅ ጉዞዋ ለመቀጠል ከቡርኪናፋሶ ጠንካራ ፈተና ይጠብቃታል። 


 

የጨዋታው አሸናፊ ሀገር በሩብ ፍጻሜው ከግብጽ ጋር ይጫወታል። 

በሌላኛው የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ምሽት አንድ ሰዓት ላይ አልጄሪያ ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም ይጫወታሉ። 

አልጄሪያ በምድብ አምስት በዘጠኝ ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቅ ጥሎ ማለፍ ገብታለች።

ተጋጣሚዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምድብ አራት በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች። 

ሀገራቱ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል።

ሞሮኮ እ.አ.አ በ1998 ባዘጋጀችው 16ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው አልጄሪያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን (በወቅቱ አጠራሯ ዛየር) 1 ለ 0 አሸንፋለች።  አብዱልቃድር ፌርሃዊ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

እ.አ.አ በ2000 በጋና በተካሄደው 22ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ሁለት ተገናኝተው ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ከ25 ዓመታት በኋላ በጥሎ ማለፍ የተገናኙት ሁለቱ ሀገራት ወደ ሩብ ፍጻሜ ለማለፍ ጠንካራ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የቡድኖቹ ጨዋታ አሸናፊ ከናይጄሪያ ጋር በሩብ ፍጻሜው ይገናኛል።  

አዘጋጇ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ ግብጽ እና ማሊ እስከ አሁን ሩብ ፍጻሜ የገቡ ሀገራት ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም