በአፍሪካ ዋንጫ ለበርካታ ጊዜ የተሰለፉ ተጫዋቾች - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ለበርካታ ጊዜ የተሰለፉ ተጫዋቾች
የአፍሪካ ዋንጫ የአፍሪካ እግር ኳስ ቁንጮ መድረክ ነው። ሀገራት በየሁለት ዓመቱ በአንድ መድረክ ተገናኝተው ዋንጫውን ለማንሳት ይፋለማሉ። ግቦች፣ ዋንጫዎች፣ ኮከብ ተጫዋቾች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች የዜና አርዕስት ሆነው ጎልተው ይታያሉ።
በአህጉራዊ መድረክ ብቃታቸው ሳይዋዥቅ ለረጅም ጊዜያት የተሰለፉ ተጫዋቾች የአፍሪካ እግር ኳስ ምልክቶች ናቸው።
ካሜሮናዊው ተከላካይ ሪጎበርት ሶንግ 36 ጨዋታዎችን በማድረግ በርካታ ጨዋታዎች ላይ ከተሰለፉ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል።
በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
ሶንግ በስምንት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ አይበገሬነቱን አሳይቷል። በተጫዋችነት ዘመኑ ሁለት የአፍሪካ ዋንጫን አንስቷል። የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖም አገልግሏል።
እንደ ሶንግ በተመሳሳይ 36 ጨዋታዎችን ያደረገው ጋናዊው አንድሬ አየው ነው። በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ስሙ ጎልቶ ከሚነሳው አብዲ ፔሌ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው አንድሬ አየው በስምንት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን አድርጓል። ቡድኑ በሁለት አጋጣሚ የፍጻሜ ተፈላሚ እንዲሆን ማድረግ ችሏል።
ጋና በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አለመሳተፏን ተከትሎ አየው የበርካታ ጊዜ የመሰለፍ ክብረ ወሰን የመስበር እድል አምልጦታል።
ግብጻዊው አህመድ ሀሰን በስምንት የአፍሪካ ዋንጫ 32 ጨዋታዎችን በማድረግ ሌላኛው ተጫዋች ነው። ሀሰን አራት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በማንሳት በስኬት ያሸበረቀ ታሪክ አለው።
ማሊያዊው ሰይዱ ኬይታ፣ ካሜሮናዊው ጀረሚ ንጂታፕ እና ጋናዊው አሳሞሃ ጊያን በተመሳሳይ 31 ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው ተሰልፈው ለሀገራቸው ተጫውተዋል።
የኮትዲቯሩ ያያ ቱሬ፣ የናይጄሪያው ጆሴፍ ዮቦ፣ የካሜሮኑ ሳሙኤል ኤቶ እና የቱኒዚያው የሱፍ ምሳክኒ በተመሳሳይ 29 ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው ተሰልፈዋል።
ኮትዲቭዋርያኑ ማክስ-አለን ግራዴል እና ቡባካር ባሪ እንዲሁም ግብጻዊው ግብ ጠባቂ ኢሳም ኤል ሃዳሪ በተመሳሳይ 28 ጊዜ ጨዋታቸውን አድርገዋል።
የኮትዲቭዋሮቹ ሲያካ ቲዬኔ እና ኮሎ ሃቢብ ቱሬ በተመሳሳይ በ27 ጨዋታዎች ላይ ተሰልፈው ተጫውተዋል።
የተጫዋቾቹ ለበርካታ ጊዜ መሰለፍ በአህጉራዊው መድረክ ለረጅም ጊዜ የመቆየት አቅም፣ አልሸነፍ ባይነት እና በጫና ውስጥ የማለፍ ብርታትን የሚያመላከት ነው።