የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት በመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል።
በስድስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 13 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 13 ጎሎችን አስተናግዷል።
ንግድ ባንክ በ12 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በውድድር ዓመቱ 11 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሶስቱ ድል ሲቀናው አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ዘጠኝ ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ13 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።
በሌላኛው መርሃ ግብር መቻል ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
መቻል እስከ አሁን በሊጉ 11 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ11ዱ ጨዋታዎች ላይ 16 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ካከናወናቸው 11 ጨዋታዎች መካከል ሶስት ጊዜ ድል ሲቀናው በአምስቱ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ነጥብ ጥሏል። ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ኢትዮጵያ ቡና በ12 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ጨዋታው መቻል ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ኢትዮጵያ ቡና ከሶስት ጨዋታዎች በኋላ ሶስት ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ነው።