በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጠናቀቃል።
በምድብ አምስት ሱዳን ከቡርኪናፋሶ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም የሚያከናውኑት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
በምድቡ ተመሳሳይ ሶስት ነጥብ ያላቸው ቡርኪናፋሶ እና ሱዳን በግብ ክፍያ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ሁለቱም ሀገራት ጥሎ ማለፍ መግባታቸውን አረጋግጠዋል።
በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ምሽት አንድ ሰዓት ኢኳቶሪያል ጊኒ ከአልጄሪያ በሙላይ ኤል ሀሰን ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በምድቡ ኢኳቶሪያል ጊኒ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዛለች። ተጋጣሚዋ አልጄሪያ በስድስት ነጥብ ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏ ይታወቃል።
ኢኳቶሪያል ጊኒ ከምድቡ መውደቋ ይታወቃል። አልጄሪያ ካሸነፈች የምድቡ መሪ ሆና ታጠናቅቃለች።
በምድብ ስድስት ጋቦን ከኮትዲቯር ምሽት አራት ሰዓት ላይ በማራካሽ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በምድቡ ሁለት ጊዜ ሽንፈት ያስተናገደችው ጋቦን ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻው አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር በአራት ነጥብ ምድቡን እየመራች ነው።
ጋቦን ከውድድሩ መሰናበቷ ይታወቃል።በአንጻሩ ኮትዲቯር ጥሎ ማለፉን መቀላቀሏን አረጋግጣለች።
በዚሁ ምድብ ሞዛምቢክ ከካሜሮን በተመሳሳይ ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአጋዲር ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሞዛምቢክ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ፣ ካሜሮን በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ሞዛምቢክ ምርጥ ጥሎ ማለፍ የገባች ሌላኛዋ ሀገር ናት።ተጋጣሚዋ ካሜሮን የመጨረሻ 16ቱን ተቀላቅላለች።
የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ከተጠናቀቁ በኋላ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከታህሳስ 25 እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳሉ።