ለትውልዱ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጉዞ በሁሉም መስክ በስኬታማነት ቀጥሏል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ለትውልዱ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጉዞ በሁሉም መስክ በስኬታማነት ቀጥሏል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ የብልጽግና ጉዞ ለትውልዱ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጉዟችን በሁሉም መስክ በስኬታማነት ቀጥሏል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ (ግሪን ሞቢሊቲ) 2025 ዐውደ ርዕይና መድረክ ዛሬ በይፋ ከፍተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በአረንጓዴ የብልጽግና ጉዞ ለትውልዱ ምቹ ሀገር የማስረከብ ጉዞ በሁሉም መስክ በስኬታማነት መቀጠሉን ገልጸዋል።
አውደ ርዕዩ እና መድረኩ ኢትዮጵያ ተፈጥሮን ለመካስና ብክለት ቀናሽ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጀመረችው ታሪካዊ ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሠረተ ስኬታማ የብልፅግና ጉዞ ላይ ትገኛለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ የትራንስፖርት ዘርፍ ታሪካዊ ሽግግር ላይ ትገኛለች - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)
ዐውደ ርዕዩ አዳዲስ የአረንጓዴ ትራንስፖርት ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት ከመሆኑም በላይ፤ በመንግሥት፣ በባለሀብቶችና በኅብረተሰቡ መካከል የጋራ ግንዛቤና ትብብር የሚፈጥር መድረክ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ለመውጣት እንደ አረንጓዴ ዐሻራና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማስፋፋት ያሉ ውጤታማ የአረንጓዴ ልማት ርምጃዎች በመንግስት እየተወሰዱ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናዊና አረንጓዴ ትራንስፖርት ዓለምን ለመምራት ዝግጁ ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዳሽ ኃይልን ከዘመናዊ ትራንስፖርት ጋር በማቀናጀትና የካርበን ልቀትን በመቀነስ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የአረንጓዴ ኢንዱስትሪ ጉዞ ቀዳሚ እያደረግናት እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።
ለትውልዱ በሁሉም መስክ ምቹ ሀገርን ለማስረከብም የአረንጓዴ ብልጽግና ጉዞ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።
ለራዕዩ መሳካት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ግለሰብና ተቋም ዘመኑን የመዋጀት የባህልና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲሁም ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እኛ ስለ አረንጓዴ ዕድገት የምንጨነቀው ስለ መጪው ትውልድ ስለምንጨነቅ ነው፤ መንግሥት ለዚህ ዓላማ ስኬታማነት የመሪነት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።